ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት ሲያገለግል የነበረው አንጋፋው ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ፣ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ከቤተሰቦቹ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ልጁ እዮብ አባተ ለኢትዮጵያ ነገ እንደገለፀው፣ ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ፣ ባደረበት ህመም ለቀናት በየካቲት 12 ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ ማለዳ አርፏል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲሰራ የምናውቀው አባተ ማንደፍሮ፣ አገሩን በውትድርና፣ በመድረክ መሪነት፣ በዜማ እና ግጥም ጸሀፊነት፣ በጋዜጠኝነትና ደራሲነት ያገለገለ ሲሆን፣ በጋዜጠኝነት በአገሪቱ ወስጥ አሉ በተባሉ የነፃ ፕሬስ ጋዜጦች እና መፅሔቶች እንዲሁም በ96.3 ኤፍ. ኤም ሬዲዮ፣ አቢሲኒያ ኢንተርቴይመንት በተሰኘ ፕሮግራሙ ላይ የቀጥታ ባለተሰጥኦዎች የድምፅ ውድድር በማዘጋጀት ለአሸናፊዎች ግጥምና ዜማ በመፃፍ እና አቀናባሪ በማፈላለግ በነፃ ነጠላ ዜማ እንዲሰሩ አድርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ጄቲቪ ኢትዮጵያ በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በፕሮግራም አዘጋጅነትና የጣቢያው ኃላፊነት፣ በአዋሽ ኤፍ ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት ሲሰራ የቆየው ጋዜጠኛው፣ በቅርቡ በድርሰት ሁለተኛ ስራው የሆነውን “ታልከል” የተሰኘ መፅሐፍ አስመርቋል።
በተለያየ ጊዜ ተደጋግሞ በሚከሰት ከፍተኛ ህመም ሲሰቃይ የነበረውና ከህመሙ ጋር እየተጋለ ስራውን ሲሰራ የነበረው ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ፣ ባለትዳር እና የአንድ ወንድና እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር።
ጋዜጠኛው በቅርቡ “ታልከል” የተሰኘ ሁለተኛ መጽሐፉን በግዮን ሆቴል ባስመረቀበት ወቅት ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
የዝግጅት ክፍላችን፣ በጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ ዜና እረፍት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለመላ ቤተሰቦቹ መጽናናትን ይመኛል።