የክቡር ዶ/ር አበበች ጎበና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው ሆስፒታል መግባታቸው ታወቀ!

የክቡር ዶ/ር አበበች ጎበና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው ሆስፒታል መግባታቸው ታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናመውደቂያ ያጡ ወገኖቻችን ሰብሳቢ የሆኑት ታላቋ የርህራሄ ተምሳሌት የክቡር ዶ/ር አበበች ጎበና፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው በጳውሎስ ሆስፒታል በኦክስጅን ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ጥቅምት 10 ቀን 1928 ዓ.ም፣ ከአባታቸው ከአቶ ጎፌ ሄዩ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወሰኔ ብሩ፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ፣ ሸበል በምትባል መንደር ይህችን ምድር የተቀላቀሉትና “አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ” እና “የእጓለማውታ መሸሸጊያ” በሚሉና በሌሎች የፍቅር ስሞች የሚጠሩት የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና፣ ካለ ስጋ ልጅ ለሺዎች እናት ለመሆን በቅተዋል። የብዙዎች ቤተሰብ ያጣውን ደስታ በእሳቸው አግኝቷል።

ብዙዎችን ከፈረሰ ቤተሰብ አውጥተው የራሳቸውን ቤተሰብ ለመመስረት እንዲበቁም አድርገዋል። ለመፈጸም ሳይሆን ለማሰብ የሚከብደውን ትልቅና ሰፊ ቤተሰብ ለዓመታት ተሸክመው ኖረዋል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ያሳደጓቸው ልጆች በአንድ ቃል “እዳዬ” እያሉ ይጠሯቸዋል። እዳዬ የሚለው ስም የልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም የሚጠሯቸው ሁለተኛ ስማቸው ነው።

የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና የአርባ አንድ ዓመታት አንጸባራቂ የብዙ ቤተሰብ ምስረታ ውጤታማ ጉዞ የተጀመረው በ1972 ዓ.ም ሲሆን፣ በመስከረም 21 የሚከበረውን የግሸን ማርያም በዓል ለማንገስ ወደ ወሎ ባቀኑበት ጊዜ በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ተከትሎ ሞት ከፊታቸው የተደቀነባቸውን ሁለት ሕፃናትን ያገኛሉ። አጋጣሚው ለወይዘሮ አበበች ሁለተኛ የህይወት ፈተና የጀመረበት ቢሆንም በሌላ በኩል ለሁለቱ ሕፃናት ብቻ ሳይሆን የሺዎችን ቤት የሚጎበኝ መልካም ዕድል የተፈጠረበትም ትልቅ የጭንቅ አጋጣሚ ነበር። በወቅቱ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ያገኟቸውን ሕፃናት ይዘው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። ምንም እንኳ በእጃቸው ሁለት ልጆችን ብቻ ይዘው ቢመጡም በልባቸው ብዙ አስበው ነበርና የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ቁጥር ከሁለት ወደ ሦስት ከሦስት ወደ አራት እያሳደጉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሃያ አንድ ያደርሱታል። ጅማሬውን በጸጋ የተቀበሉት ባለቤታቸው አቶ ከበደ ኮስትሬ ደግሞ ነገሩ እየከበዳቸው ሲመጣ ወደ ምክርም ወደተግሳጽም ገቡ፤ ወይዘሮ አበበች ግን አሻፈረኝ አሉ። ለሽምግልና የተሰበሰበውም ቤተ ዘመድ ተናግሮ ባለመደመጡ በአንድ ድምፅ እንዲህ ዓይነት ሥራ የጤና ሳይሆን የበሽታ ስለሆነ “አበበች አብዳለች!” ጠበል ትግባ የሚል ምክር ያቀርባል። በዘመኑ ሀብታም ከሚባሉ ሰዎች ተርታ የሚሰለፉና ጥሩ የሚባል ህይወት ይኖሩ የነበሩት የክብር ዶ/ር አበበች ምላሽ ግን በተቃራኒው ነበር። በውሳኔያቸውም መሰረት ከዚያ ከረሀብ ከዚያ ከስቃይ ያወጧቸውን ልጆች መርጠው ትዳራቸውንም ሀብታቸውንም ትተው ከሕፃናቱ ጋር በአንድ የሳጠራ ጎጆ ዛሬ ለመቶ ሺዎች ቤተሰብ የሆነውን ኑሮ በድፍረት ያለማንም ረዳት “ሀ” ብለው ጀመሩ። የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል የሕፃናት ማቆያ ድርጅትም በዚያው መሰረቱን ለመጣል በቃ።

የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ማዕከል ባለፉት አርባ አንድ ዓመታት፣ ከሦስት ሺ አምስት መቶ በላይ ሕፃናትን የልጅነት ጊዜያቸውን በማቆያው እንዲያሳልፉ በማድረግ ለወግ ማዕረግ አብቅቷል። በአሁኑ ወቅትም በአመት ከ7 ሺ 500 በላይ ሕፃናትን በተለያዩ ፕሮግራሞች በአዲስ አበባ፣ ጉደርና ቡራዩ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። 34 ሕፃናት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በማህበሩ ስር እየኖሩ ናቸው። የአደራ ቤተሰብ በሚለው የድጋፍ ዓይነትም ጥናት ተሠርቶ ወጪ ተችሎ ልጅ የሚሰጣቸው ቤተሰቦችም አሉ።

የክብር ዶ/ር አበበች በታሪካቸው ለአገልግሎታቸው አንድም ቀን ደመወዝ ተቀብለው የማያውቁ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጌጣ ጌጥና ልዩ ልዩ ስጦታዎች ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ቢበረከትላቸውም አንዱንም ለራሳቸው ጥቅም አውለው አያውቁም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሽልማቶችን ያገኙም ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከእንግሊዝ ሀገር ወርልድ ቢዝነስ አዋርድ፣ ሁለት ጊዜ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የክብር ዶክትሬት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሞያቸው የላቀ አስተዋጽኦ ስላበረከቱ 50ኛ የኢዩቤልዩ ሜዳሊያ፣ ማዘር ቴሬዛ ኦፍ አፍሪካ አዋርድ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደር በቅርቡ ያስጀመረውን የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል በስማቸው እንዲጠራ መሰየሙ የሚጠቀሱ ናቸው።

በዛሬ ጊዜ የማዕከሉ እንቅስቃሴም ሆነ የተጠቃሚው ቁጥር በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን የክብር ዶክተር አበበች ጎበና የመዘንጋት የጤና እክል ገጥሟቸው ከቤት ለመዋል ተገደው ነበር። ከአንድ ስማቸውን ቀይረው ከሚጠሯቸው የአክስታቸው ልጅ በቀርም የሚያስታውሱት ነገር የለም። ለህመማቸው መንስኤው ደግሞ እርጅና ብቻ ሳይሆን በየወቅቱ ይገጥማቸው የነበረው ጭንቀት ነው። አሁን ደግሞ እኒህ ታላቅ እናት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በጳውሎስ ሆስፒታል በኦክስጅን ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍል፣ እኒህ ታላቅ ባለታሪክና ሩህሩህ እናት ከገጠማቸው ህመም አገግመው በጤና እንዲወጡ ከልብ ይመኛል።

LEAVE A REPLY