ምርጫ የማይካሄድባቸውን 26 ቦታዎች ምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ!

ምርጫ የማይካሄድባቸውን 26 ቦታዎች ምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በ26 ምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ የመስጠት ተግባር እንደማይከናወን አስታወቀ።

ቀደም ሲል በግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በእለቱ የድምጽ አሰጣጡ የማይከናወንባቸው ምርጫ ክልሎች መኖራቸውን እና ምክንያታቸውን አብራርቶ የነበረውና ስለምርጫ ክልሎቹ በየጊዜው ግምገማ እያደረገ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እንደሚሰጥ የገለጸው ምርጫ ቦርድ፣ ትናንት ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ በማብራሪያውም 26ቱ የምርጫ ክልሎች በአራት የሀገሪቱ ክልሎች የሚገኙ መሆናቸው ጠቅሷል።

“እነሱም በቤንሻንጉል ክልል 4 ምርጫ ክልሎች፤ በኦሮሚያ ክልል 7 ምርጫ ክልሎች፤ በአማራ ክልል 8 ምርጫ ክልሎች ናቸው። እንዲሁም፦ በደ/ብ/ብ/ህ ክልል 7 የምርጫ ክልሎች በድምሩ 26 የምርጫ ክልሎች ናቸው” ያለው ቦርዱ “ከዚህ በተጨማሪም፤ በሶማሌ ክልል ከ14ቱ ምርጫ ክልሎች 11ዱ ምርጫ ክልሎች ምርመራ ላይ ይገኛሉ፣ በተጠቀሱት 11ዱ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ድምጽ የመስጠት ሂደት ለማካሄድ አስቸጋሪ ይሆናሉ” ብሏል።

በ11ዱ ምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጠት ሊከናወንባቸው የሚችል ምርጫ ክልሎች ካሉ ምርጫ ቦርድ “ለይቶ የሚያሳውቅ” መሆኑንና በየጊዜው በሚያደርጋቸው ግምገማዎች የሚገኙ ውጤቶችንም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ቦርዱ አስታውቋል።

LEAVE A REPLY