ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ጄኔራል ሳአረ መኮንንን እና ሊጠይቋቸው ከቤታቸው የተገኙት ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራ አበራን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር እንዲቆይ የተደረገው የአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡን ጉዳይ የሚመለከተው፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ በተከሳሹ ላይ ዛሬ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት፣ ተከሳሹ “ወንጀሉን አልፈጸምኩም” ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱና ይህንኑ ተከትሎም ዐቃቤ ህግ የጄኔራል ሰአረን ባለቤት ኮሎኔል ፅጌን እና የጄኔራል ሰአረ አጃቢዎች ጨምሮ በአጠቃላይ 7 የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር፣ ተከሳሹ እንዲከላከል በፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረትም ተከሳሹ ሶስት የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ሲከራከር የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ በተገቢው ማስተባበል አለመቻሉንና መዝገቡንም በጥልቀት መመርመሩን ገልጾ “የዐቃቤ ህግ ማስረጃ ተከሳሹ ወንጀሉን መፈጸሙን ያረጋገጠ ነው” በማለት በሙሉ ድምጽ ጥፋተኛ ሲል በይኗል፡፡
ችሎቱ፣ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊትም ተከሳሹ የሚያቀርበውን የቅጣት ማቅለያ ለመመልከት፣ ለሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ተገኝቶ የነበረው ተከሳሹ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ በግራ ጭንቅላቱ ላይ እና በእግሩ ላይ በደረሰው ጉዳት የአንድ አይኑ እይታ መጋረዱን የተናገረና ሲራመድም እያነከሰ የነበረ ሲሆን፣ ይህን የተገነዘቡት ዳኞችም “ስላመመህ ቁጭ ብለህ ተከታተል” የሚል ፈቃድ በመስጠታቸው ተቀምጦ ፍርዱን እንዲከታተል መደረጉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ተከሳሹ፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ጄኔራል ሰአረ መኮንን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከነበሩት ከአቶ ታከለ ኡማ ጋር ችግኝ ተክለው ከተመለሱ በኋላ፣ 12 ሰአት ገደማ በባህርዳር በእነዶ/ር አንባቸው ላይ ግድያ መፈፀሙን ተከትሎ በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው ሆነው በስልክ አመራርነት እየሰጡ ባሉበት ወቅት፣ ወደ ቤታቸው ሊጠይቋቸው መምጣታቸው ከተነገረው ከሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራ ጋር በሽጉጥ ተመተው መገደላቸው በይፋ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን “የአማራ ክልል መንግስትን በሀይል ለማፍረስና የፌዴራል መንግስትን ለመቆጣጠር የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ተከሳሹ በግንቦት ወር 2011 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ከጄኔራል አሳምነው ፅጌ ጋር በመገናኘት ተልዕኮ ተቀብሎ በወንጀሉ ተሳትፏል። በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀናለ 35 /38 እንዲሁም 238 በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተሳትፎ ህገመንግስቱን በመሻርና በህገመንግስታዊ ስርአቱ አደጋ ፈጽሟል” በሚል መከሰሱ ይታወሳል፡፡