ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገኘውና ለከተማዋ ነዋሪዎች ልዩ የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ኤድና ሞል ከነሙሉ የመዝናኛ ቁሶቹ በሐራጅ ሊሸጥ መሆኑ ተሰምቷል።
የኤድና ሞል ባለቤት የሆኑት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ በስማቸው በተቋቋመው የኮንስትራክሽን ድርጅት (ተክለብርሐን አምባዬ ኮንክትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር) አማካኝነት ኤድና ሞልን በመያዣነት በመጠቀም ከባንክ የተበደሩትን ብድር ባለመመለሳቸው ብድሩን ያበደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድሩ መያዣ የሆነውን ኤድና ሞልን በሐራጅ ለመሸጥ እንደተገደደ ያመለከቱ የመረጃ ምንጮች ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከባለቤቱና ከሌሎች የድርጅቱ ሀላፊዎች ጋር አመታትን የፈጀ ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።
አቶ ተክለብርሃን አምባዬ በስማቸው ባቋቋሙትና ተክለብርሐን አምባዬ ኮንክትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተባለ ድርጅታቸው አማካኝነት በርካታ የመንገድና የህንፃ ግንባታ ስራዎችን በመስራት የሚታወቁ ቢሆንም ከለውጡ በፊት ከነበረው መንግስት ሰዎች ጋር በነበራቸው የቅርብ ወዳጅነት ተገቢ ያልሆኑ ጥቅሞችን የማግኘት ተግባር ውስጥ በመሳተፍም የሚታሙ ናቸው።