ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአፍሪካ ሕብረት አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ ትናንት ማምሻውን ባሰራጨው መግለጫ፣ ከሕብረቱ አባል አገራት የተውጣጡና ስምንት አባላት ያሉት የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን፣ ግንቦት 25 እና 26 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱን አስታውቋል።
የሕብረቱ የአጭር ጊዜ ታዛቢዎች ቡድን ከምርጫው አንድ ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ያመለከተው ይኸው የህብረቱ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን ግብዣ ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ ምርጫውን የሚታዘቡ የአፍሪካ ሕብረት የአጭርና የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን ስምሪት ማድነቃቸው አስታውሷል።
ታዛቢዎቹ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚካሄደው 6ኛውን አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት የሚኖረውን የፖለቲካ ከባቢ አየር፣ የምርጫው ሕጋዊ ማዕቀፎች፣ የምርጫ ዝግጅትና አስተዳደሮች ግልጽነትና ውጤታማነትን እንዲሁም የምርጫ ቅስቅሳ ሁኔታን የመታዘብ ስራ እንደሚያከናውኑም በህብረቱ መግለጫ ተመልክቷል።