ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች፣ በምርጫው እንዲሳተፉ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔ፣ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ በፍትህ ስርዓቱ ሂደት ላይም ትልቅ ተስፋ የፈጠረ ነው መሆኑን የፓርቲው የቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ ገልጸዋል።
“ፍርድ ቤቱ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር የሚገኙ የባልደራስ አመራሮችን ለምርጫው በዕጩነት እንዲመዘገቡ ውሳኔ ማስተላለፉ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አዲስ ነገር ይዞ የመጣና በተጠርጣሪነት ተይዘው በምርጫ መወዳደር ለሚፈልጉ ዜጎች ለወደፊቱም በር የከፈተ ነው” ያሉት የቢሮ ኃላፊው “በኢትዮጵያ ህግ አንድ በተጠርጣሪነት በጸጥታ ቁጥጥር ስር የሆነ ሰው በምርጫ መወዳደር እንደሚችል ተቀምጧል። ይህን የሚያስተጓጉል ኃይል ቢመጣ ግን ፍርድ ቤት ለዜጎች የመምረጥ እና መመረጥ መብት እንደሚቆም ያሳየ ውሳኔ በባልደራስ አመራሮች ላይ ተላልፏል” ብለዋል።
ውሳኔውም በፍትህ ስርዓቱ ሂደት ላይ ትልቅ ተስፋ የፈጠረ ነው። ለወደፊትም ተቋማት ህግን አክብረው እንዲጓዙ ያስተማረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በፍርድ ሂደቱ ለለውጥ የሚታገሉ ዳኞች መኖራቸውን አይተናል። በአንጻሩም አቃቤ ህግ የሚያቀርባቸው ቀና ያልሆኑ ክሶች አሉ። ከዚህ የምረዳው የፍትህ ተቋሙ ትግል ላይ መሆኑን ነው። ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዜጎችን የመምረጥ መመረጥ መብት አክብሮ ይህንን ፍርድ በመስጠቱ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ስሜት ቀና እንዳደረገ ይሰማኛል። በውሳኔው መሰረት አንዳንድ ሰዎች በፍትህ ስርዓቱ እንዲህም አይነት ነገር አለ እንዴ የሚል በጎ ስሜት ተፈጥሮባቸዋል። ውሳኔው ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ህግ እና ፖሊስ የመሳሰሉ አካላት የዜጎችን መብት ባስከበረ መልኩ መራመድ እንዳለባቸው ያሳየ እና ተስፋ የፈነጠቀ ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ የተናገሩት አቶ ገለታው በቀጣይም ዳኞች ለሀቅ እና ለእውነተኛ ፍትህ የቆሙ መሆናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።