ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ የቤት ሠራተኛዋን ከ1 ዓመት በላይ ከቤት እንዳትወጣና የፀሃይ ብርሃን እንዳታገኝ በማድረግ፣ ምግብ በመከልከል በአሰቃቂ ሁኔታ ከፍተኛ ድብደባ ስትፈፅም የነበረች ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ የሴቶችና ህፃናት ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ኤርሚያስ ጋቸኖ እንደገለፁት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ስሙ ሲ.ኤም.ሲ አልታድ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንዲት ግለሰብ በቤት ሠራተኝነት የቀጠረቻትን የ20 ዓመት ወጣት በተደጋጋሚ በመደብደብ፣ ምግብ በመከልከል፣ በር በመቆለፍ ከቤት እንዳትወጣ እና የፀሃይ ብርሃን እንዳታይ እያደረገች ስትበድላት ቆይታ የቤቱ አከራይ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራባት ይገኛል።
ጥሩአለም ደጉ የተባለችው የግል ተበዳይ ወጣት፣ በቤት ሰራተኝነት ከተቀጠረች ጊዜ ጀምሮ ለ1 አመት ከ2 ወር ያህል ከባድ የሆነ ስቃይ ሲደርስባት እንደነበር በመግለፅ ፖሊስ ደርሶ ህይወቷን እንዲያተርፍላት ለቤቱ አከራይ በአጋጣሚ ባገኘችው የመስኮት ቀዳዳ ወረቀት ፅፋ መስጠቷን የገለጹት ኢንስፔክተር ኤርሚያስ ጋቸኖ፣ የቤቱ አከራይ አቶ ዮሐንስ ኃ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ሰራተኛዋን የተቀጠረች ቀን ብቻ ማየታቸውንና በተደጋጋሚ ያስቀጠራትን ደላላ ስለ ልጅቷ ጉዳይ መጠየቃቸውን ተናግረው በወረቀት ተፅፎ በመስኮት የተወረወረላቸውን መልዕክት ካገኙ በኋላ ለአቅራቢያቸው ፖሊስ ጣቢያ መጠቆማቸውን አስረድተዋል።
በደል አድራሿ ተጠርጣሪ ፖሊስ ወደ ስፍራው ሲደርስ፣ ሰራተኛ እንደሌላት በመናገር ልትደብቃት ብትሞክርም ሰራተኛዋ ግን አልጋ ውስጥ ሆና ስትጮኽ ፖሊስ በመስማቱ ከስቃይ ሊያድናት እና አሰሪዋንም በቁጥጥር ስር ሊያውላት መቻሉን የተናገሩት ረዳት ኢንስፔክተሩ፣ ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለፀጥታ አካላት ሊጠቁምና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል አካባቢውን በንቃት ሊመለከት እንደሚገባም አሳስበዋል።