ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም አካባቢውን ወደነበረበት መልሶ ለማቋቋም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ማደራጀት አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ እንዲሁም “የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ማደራጀት ከተቻለ ከተማዋን መልሶ ለመገንባት ጠቀሜታ ይኖረዋል” በሚል ታምኖበት የተከናወነ እንደሆነና የተደረገው ድጋፍም 10 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ሚኒስትሩ አስታውቋል።
ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው የቁሳቁስ ድጋፉ መሥሪያ ቤቶችን ሥራ ለማጀመር እንደሚጠቅማቸውና ባለፉት ቀናትም በከተማዋ የመንግሥት አገልግሎትን ለማስጀመር ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፣ ከሰኞ ግንቦት 30/2013 ዓ.ም ጀምሮ የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙና የከተማዋ ነዋሪዎች በአሉባልታ ሳይሸበሩ ወደነበሩበት አካባቢ በመመለስ ከተማዋን ለመገንባት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ አጣዬ ወደሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ደውለን ባገኘነው መረጃ፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ ጽ/ቤቶችን ጨምሮ አንዳንድ የመንግስት መ/ቤቶች ክፍት መሆናቸውንና አብዛኛዎቹ ፋይል በማደራጀትና ቦታ በማስተካከል ስራ ላይ በመሆናቸውም መደበኛ አገልግሎታቸውን ጀምረዋል ማለት እንደማይቻል ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና፣ በርካታ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች “አሁንም በአካባቢው የጸጥታ ችግር ሊከሰት ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቅሰው “ከማንኛውም ሥራ በፊት ሰላም እንዲረጋገጥ” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡