ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ሲሸጡ በተገኙ 24 ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
የባለስልጣ መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት ስጋት የሆነው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር በመደባለቅ ለገበያ ማቅረብ መሆኑን ገልጸው፣ ከባዕድ ነገር ጋር በመደባለቅ ለገበያ እየቀረቡ ካሉ ምግቦች መካከል እንጀራ፣ ቅቤ፣ በርበሬና ማር እንደሚገኙበት አመልክተዋል።
“ምግቦቹ ወቅት ጠብቀው ለገበያ የሚቀርቡ ናቸው። የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተደረገ ክትትልም በአዲስ አበባ 24 ድርጅቶች ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው በመገኘታቸው ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በአራት ክፍለ ከተሞች በተደረገ ክትትል 3 ሺህ 360 ኪሎ ግራም ቅቤ፣ 480 ኩንታል በርበሬ እና ከ1 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ከቅቤ ጋር ለማደባለቅ የሚውሉ የአትክልት ቅቤና የፓልም ዘይት መያዙን ገልጸዋል።