ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለአንድ ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ የገቡት ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኢትዮጵያ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እንዲሁም ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በወቅታዊ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት መጀመራቸው ተነግሯል።
የፕሬዚዳንት ኡሁሩን ወደኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት “የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ወንድሜ ኡሑሩ ኬንያታን የቴሌኮም ፍቃድ ስምምነትን በምንፈራረምበት በዛሬው ታሪካዊ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ ለማለት እወዳለሁ፡፡ #ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እና 1 ቢሊዮን ችግኞችን ለጎረቤቶቻችን በማዘጋጀት የ #አረንጓዴዐሻራ መርሐ ግብርን ወደ ቀጣናው በምታስፋፋበት ወቅት ላይ ነን። ይህንን መሠረት አድርገን ችግኞችን በጋራ ተክለናል” ብለዋል።
በተያያዘ፣ የኬኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪይቸል ኦማሞ፣ ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸውና ኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር በሁለትዮሽ እና በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
አምባሳደር ሬድዋ፣ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንዲሁም የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሚኒስትሯ ማብራሪያ መስጠታቸውን የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ቀጣዩ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ ከማድረግ ጀምሮ ሥራዎች መከናወናቸውን፣ በምርጫው 50 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ መሆኑን፣ ከሀገሪቱ ለመምረጥ የሚችሉ ዜጎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ መመዝገባቸውን እንደገለጹ አመልክቷል።
በተጨማሪም፣ ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተም ሱዳን ወደ ኢትየጵያ ልዑላዊ ግዛት መግባቷንና በኢትዮጵያ በኩል በሀገራቱ መካከል ቀደም ሲል በተቋቋሙ የጋራ ድንበር ኮሚቴዎች አማካይነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ሊያገኝ የሚችል መሆኑን ኢትዮጵያ እንደምታምን፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በኢትዮጵያ በኩል በመጀመሪያ የግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ ስምምነት ላይ በመድረስ በሌሎች የውኃ ስምምነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ ግን ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱና የሌሎችንም የተፋሰሱ ሀገራት ተሳትፎ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር ቀጥሎ መታየት እንደሚገባው በኢትዮጵያ በኩል የተያዘ አቋም መሆኑን፣ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በዋናነት በመንግሥት በኩል እየቀረበ መሆኑንና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ ተቋም ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የጋራ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን፣ አንዳንድ አካላት በክልሉ ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ ገንቢ ሚና ከመጫወት ይልቅ ከእውነት የራቁ እና የተጋነኑ መረጃዎችን በማቅረብ በመንግሥት ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ላይ መጠመዳቸውን አምባሳደር ሬድዋን በውይይቱ ወቅት በዝርዝር ማስረዳታቸውንም የሚኒስቴሩ ጽ/ቤት ገልጿል።
ኬንያ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ጎረቤት ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። ሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዳላቸውና በአትሌቲክስ ተመሳሳይ ጥንካሬ ያላቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡ በሀገራቱ መካከል በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ትብብሮች ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ምቹ ሁኔታ አስረድተዋል።
በሀገራቱ መካከል በርካታ ስምምነቶች መፈረማቸውም ግንኙነቱ እየተጠናከረ ለመምጣቱ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ስምምነቶቹ ያሉበትን ደረጃ በመለየት ተግባራዊታቸውን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ተጨማሪ የትብብር መስኮችን መጨመር እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል።
የኬኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ኬኒያ ባላቸው ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት የተፈራረሟቸውን በርካታ ስምምነቶች ተግባራዊነት በማፋጠን ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ጠቅሰው፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ ውይይቶችን በማካሄድ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምክር እንዲሚያስፈልግ የተናገሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይረዳ ዘንድም እስካሁን የተፈረሙ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተግባራዊነት ለማፋጠን አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመለየት በሁለቱም ወገን በተሰየመ የጋራ ኮሚቴ አማካይነት እንዲቀርብ መግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡