ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኤርትራ መንግስት “አሜሪካ የህወሓት አመራሮችን ትደግፋለች” ሲል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ክስ ማስገባቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ደግሞ “በርካታ የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አካባቢዎች ረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው” ብለዋል።
“አሜሪካ ላለፉት 20 አመታት በላይ፣ በትግራይ ክልልና በቀጠናው ጦርነት እንዲነሳ ስትሰራ ቆይታለች። አሁንም የባይደን አስተዳደር ቀጠናውን ወደ ትርምስ ለማስገባት እየሰራ ይገኛል” ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ የተናገሩት የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ፣ ዋሽንግተን በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳ “አግባብነት የሌለው ነው። የባይደን አስተዳደር እየሄደበት ያለው መንገድም ህወሓት ዳግም አንሰራርቶ ወደ ስልጣን እንዲመጣ በማሰብ ነው” በማለት ኤርትራ ለፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ ክስ ማስገባቷን አስታውቀዋል።
“የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለሚካሄደው ጦርነት ኤርትራን ተጠያቂ ማድረጉ መሠረተ ቢስ ነው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኤርትራ መንግስት ትናንት ሰኞ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፈውና ለምክር ቤቱ በተሰራጨው ደብዳቤ “የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በክልሉ ጣልቃ መግባቱና ማስፈራራትን መምረጡ ተጨማሪ ግጭትን እና አለመረጋጋትን ያስከትላል” ማለቱንም አመልክተዋል ።
በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አካባቢዎች ረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን አመልክተው “የትግራይ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው” በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት አሳስበዋል፡፡
“የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ለመግታት ሰብአዊ እርዳታ ማዳረስ እንዲሁም በቂ ፈንድ ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት ዋና ጸሃፊው “አሁን የሚከናወኑ ተግባራት ለበርካታ ሰዎች የመኖርና አለመኖር ጉዳይ መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው” ሲሉም በመልእክታቸው ገልጸዋል።