ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር በወፍ አርግፍ ከተማ የአሸባሪው ሕወሃትን ግፍ የሚያወግዝና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰልፍ ዛሬ የተካሄደ ሲሆን፣ በሰልፉ መልእክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማይመስለው ማንነት ተሰጥቶትት በግፍ ሲንገላታ ቆይቷል፣ አማራ ነን ማንነታችን ይመለስ እያለ ሲጠይቅ ነበር” ብለዋል።
ለማንነት ሲባል ብዙ ወገኖች መስዋእትነት ሆነዋል። የሕዝብን ጥያቄ ለመስማት ፈቃደኛ ያልነበረው አሸባሪው ሕወሃትም በሕዝቡ ትግል ወድቋል። ዓለም ወልቃይት ጠገዴን ሊሰማ ይገባል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጥያቄዬን ስሙኝ ሲል ኖሯል፣ የአሜሪካ መንግሥትም የወልቃይት ጥያቄን ያውቃል፣ ነገር ግን ለራሱ ጥቅም ብቻ ስለሚቆም የወልቃይትን ጥያቄ ወደጎን በመተው ለአሸባሪው ወግኗል፣ ይህን አቋሙን ማስተካከል ይገባዋል” ያሉት ኮ/ል ደመቀ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሰላሳ ዓመታት በአሸባሪው ቡድን የተገዛው በፈቃዱ አለመሆኑን በመጥቀስም “አማራ ነፃ ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ነው፣ ጭቆናን የመሸከሚያ ትክሻ የሌለው መሆኑን ደጋግመን እንነግራችኋለን፣ ከጭቆና ተላቀናል” ብለዋል።