ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ቴሌኮም የ40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ በሂደቱ ተሳታፊ መሆን የሚፈልጉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ Expression of Interest (EOI) ከነገ ሰኔ 08 ቀን 2013 ጀምሮ ማስገባት እንደሚችሉ ተገለጸ።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ አማራሮች ኢትዮ-ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ምዕራፍ የተጠናቀቀ መሆኑን ዛሬ ያስታወቁ ሲሆን፣ ሂደቱ የዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከግንዘቤ ያስገባ ከመሆኑ ባለፈ በፋይናንስ፣ በንግድ ሥራ ዕቅድ ፣ በሕግ እና ታክስ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራን በተመለከተ በማማከር ረገድ ዴሎይት እንደ ዋና የግብይት አማካሪ ሆኖ የሚሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የፍላጎት መግለጫው ለአንድ ወር የሚቆይና ዝርዝሩም በገንዘብ ሚኒስቴር እና በመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ድህረ ገጽ ላይ እንደሚለቀቅ የገለጹት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተወዳዳሪ ባለሀብቶች በአፍሪካ ትልቁ በሆነው ኢትዮ-ቴሌኮም በከፊል የማዛወር ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ መቅረቡንም አመልክተዋል።
የኢፌዲሪ ገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የመወዳደሪያ ፍላጎት መግለጫውን ተከትሎ ተጫራቾች የመወዳደሪያ ዕቅድ ጥያቄያቸውን (Request for Proposal (RFP)) እንደሚያስገቡ ገልጾ “ይህም አጠቃላይ ሂደቱ ወቅቱን የጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና የተስተካከለ አሰራረርን በመያዝ የሚገለጽ ይሆናል” ብሏል።