ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌዴራልና የክልል የደህንነትና የፀጥታ አካላት ግብረ-ሐይል “የፌዴራል እና የክልል የጸጥታና ደህንነት አካላት ቅንጅታዊ ስራ ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት” በሚል ምክክር እያካሄዱ መሆኑና ከምርጫው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ የወንጀል ተግባራትን በማጣራት ፖሊስ 147 የምርመራ መዝገቦችን አደራጅቶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቅረቡ ተገለጸ!
የፌዴራልና የክልል የደህንነትና የፀጥታ አካላት ግብረ-ሐይል በጀመረው የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ “የፌዴራልና የክልል ጸጥታ ተቋማት የሀገራችንን ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ ሀላፊነት ወስደው እየሰሩ ናቸው። የሀገርን ጥቅሞችን ማረጋገጥ የሚቻለው በፌዴራል፣ በክልል፣ በአካባቢ መስተዳድሮችና በህዝቡ ዘንድ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶችን መጠቀም ሲቻል ነው” ብለዋል፡፡
“ምርጫውን እና የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚሰሩ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች አሉ” ያሉት አቶ ተመስገን “በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ስልጣን ያጡ ሀይሎች መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ምርጫ እንዳይካሄድ ከተካሄደም የውሸት ወሬ በመንዛት ቅቡልነት እንዳያገኝ እየሰሩ መሆናቸውን ደርሰንበታል። የደህንነት መስሪያ ቤቱም ክትትል እያደረገ ነው” ሲሉም የገለጹ ሲሆን፣ ምክክር ላይ የሚገኘው የጋራ ግብረ ሀይሉ የሀገሪቷን ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ “ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከምርጫ ጋር በተያያዘ 315 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለውና 147 የምርመራ መዝገቦች ተደራጅተው፣ 334 የሰውና የሰነድ ማስረጃ ተዘጋጅቶና ተሰብስቦ 58 መዝገቦች ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ተልከዋል። ከነዚህ ውስጥ 36ቱ መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ በምርመራ ላይ ይገኛሉ” በማለት ይህን መሰሉ ስራ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዝርፊያ፣ ድብደባ፣ ስርቆት፣ የምርጫ ቁሳቁስ ማቃጠል፣ በተከለከሉ ቦታዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ፖስተር መቅደድ፣ ደጋፊን ማዋከብ፣ የምርጫ ካርድ ማጭበርበር፣ መራጮች የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ ማድረግና የምርጫ ጣቢያ ማቃጠል፤ በአጠቃላይ የተፈፀሙት የወንጀል አይነቶች መሆናቸውንም ምክትል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።