5 ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ! ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በምርጫው እንደማይሳተፍ አሳወቀ!

5 ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ! ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በምርጫው እንደማይሳተፍ አሳወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ሕብር ኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ “አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉበት የሚከናወን ምርጫ ሀገር በጉጉት ወደምትጠብቀው ሥርዓት አያሸጋግርም!” በሚል ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ እስካሁን ሲከናወን በቆየው የምርጫ ሂደት ላይ ያላቸውን ቅሬታ በዝርዝር አስታውቀዋል።

በምርጫው ሂደት ከመነሻው ጀምሮ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አምስቱ ፓርቲዎች ” …ምንም እንኳ በትክክለኛው ትርጉሙ ምርጫ የሚባልና የምርጫ መስፈርትን ከብዙ በጥቂቱም ቢሆን የሚያሟላ ነገር ሀገራችን አከናውና ባታውቅም ወደዚህ ምርጫ ስንገባ የተገባው ቃል እውን ሊሆን የሚችል ተስፋ ይዘን ነው፡፡ ምርጫ በአንድ ጀንበር /በምርጫው ቀን ብቻ/ የሚከናወን ሳይሆን የምርጫውን ነፃና ፍትሃዊነት ለመገምገም የምርጫውን ሂደት ከመነሻ እስከ ፍፃሜው በወጥነት መመልከትን የግድ ይላል” ሲሉ አመልክተዋል።

“ከዚህ አኳያ በአንዳንድ ቦታዎች በሠላም እጦት ምክንያት በሌሎች ደግሞ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በምርጫ አስፈፃሚው አካል ችግር እንደታየበት በመጤኑ ትንሽ በማይባል የሀገራችን ክፍል ምርጫው እንዲዘገይ የተደረገባቸው አካባቢዎች ቁጥር ቀላል የማይባል ቢሆንም ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄድባቸዋል በተባለው የሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የምርጫው ቀን እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ያለፍንባቸውን የቅድመ ምርጫ ሂደት ውጣ ውረዶች መራጩና የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል” በማለትም ፓርቲዎቹ ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ ቅሬታቸውን ከዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርበዋል፤

በዚሁ መሠረት፡-በእጩዎች ምዝገባ ወቅት፡- በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሆን ተብሎ እጩዎችን ላለመዝገብ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ ቀላል የማይባል እንግልት በእጩዎቻችን ላይ ደርሷል፤

በመራጮች ምዝገባ ወቅት፡- የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በአብዛኛው ያልተጀመረ ሲሆን/ምንም እንኳ ይህን ለማካካስ የምዝገባ ቀን ማራዘሚያ ቢደረግም / ከተጀመረም በኋላ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ለምዝገባ ሲመጡ ሆን ብሎ በማጉላላት መራጮች እንዳይመዘገቡ የተሰሩ ሥራዎች፤ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚመዘገቡ መራጮች ቁጥር 1500 ብቻ መሆኑ አንዳንድ ቦታ ላይ የተፈቀደው ቁጥር ሞልቷል በሚል ምክንያት መራጮች እንዳይመዘገቡ እንቅፋት መሆኑ፤

የተመዝጋቢዎች ቁጥር የተቀመጠው ጣሪያ ላይ በመድረሱ መራጮች ሊመዘገቡ አለመቻላቸውም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ ምንም እንኳ ንዑስ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ አቅጣጫ ቢቀመጥም ንዑስ ጣቢያዎች በቶሎ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው፤ አንዳንዶች የምርጫ ጣቢያዎች እና ንዑስ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ቦታ በተለይ በአዲስ አበባ ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ተግባር ማከናወኛ ከሞራል አኳያ የሚመጥኑ ባለመሆናቸው የመራጮች ደስተኛ ሆኖ ወደእነዚህ ጣቢያዎች ሄዶ አለመመዝገብ፤ እነዚህና የመሳሰሉት በጉልህ የታዩ ችግሮች በመራጭነት ሊመዘገብ የሚችለውን ሕዝብ በሚፈለገው መጠን እንዳይመዘገብ ያደረገው መሆኑ፤

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት፡- ምርጫው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሙሉ በሚባል መልኩ /አዲስ አበባ ብቻ ሲቀር/ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ በከፍተኛ ችግር የታጀበ መሆኑ እነዚህም፡ በእጩዎች ላይ ግድያ መፈጸም፣ የግድያ ሙከራ እና ድብደባ መፈፀም፤ እጩዎችን ከህግ አግባብ ውጭ አስሮ ማንገላታት፤ ለምርጫ ቅስቀሳ ሲወጣ መቀስቀስ አትችሉም በማለት ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት የተሰማራን ቅስቀሳ ተሽከርካሪና የድምፅ ሲስተም አግዶ በማዋል የምርጫ ቅስቀሳን በማስተጓጎል ለገንዘብ ኪሣራ መዳረግ፤ እጩዎች እንዳይቀሰቅሱ የግድያ ዛቻና ማስፈራራት በማድረስ የማሸማቀቅ ሥራ መስራት፤ እጩዎችን አስገዳጅ በሆነ ምልኩ ያለደመወዝ እረፍት እንዲወጡ ማስገደድ፤ እጩዎች ከእጩነት ራሳቸውን እንዲያገሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጫና ማድረግ፣ የምርጫ ምልክት ያለባቸውን የቅስቀሳ ባነር ማውረድ፣ መቅደድ እና በምትኩ የብልጽግናን ምልክት መስቀል ወዘተ በስፋት የተስተዋሉና እየተስተዋሉ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ከመፍታት አኳያ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ፓርቲዎቹ በቅርበት በመሥራት መፍትሄ ለማግኘት በተናጠል ጥረት ያደረግን ሲሆን በዚህ ረገድ የተወሰኑትን ችግሮች ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ የተቀመጠው በአንድ የምርጫ ጣቢያ የተመዝጋቢዎች ቁጥር ጣሪያ ቢነሣ የተከፈቱት ተጨማሪ ንዑስ ጣቢያዎች ለሕዝቡ በቀላሉ ተደራሽ ሆነው ምዝገባውን ማከናወን ቢቻል ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ መመዝገብ ይቻል እንደነበር በመግለጽ የምርጫ ቀኑ አስቀድሞ ከተያዘው ከግንቦት 28 ቀን ወደ ሰኔ 14 ቀን መገፋትን ተከትሎ የመራጮች ምዝገባ ቀን ለተወሰነ ጊዜ ክፍት እንዲደረግ
ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የዘረዘርናቸው ችግሮች በአጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በብዙ ችግሮችና ውጣ ውረዶች የተሞላ እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ሕዝባችን ይህን እንዲያውቅ ከማድረግ ጎን ለጎን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከእኛ የምትጠብቀውን በግልጽ በመረዳት ሥልጣን ላይ ተጣብቆ ለመቆየት ከመፍጨርጨር ይልቅ በቃል የተነገረውን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እውን የማድረግ ነገር ከቃል በዘለለ በቀጣይ ቀሪ ጥቂት ቀናትና በመርጫ ወቅት ገዥው ፓርቲና የመንግሥት የተለያዩ የአስተዳደር አካላት ይህን በተግባር እውን የማድረግ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅና ይህንኑ ለግብር ከፋዩ ሕዝብ ማሳየት እንደሚገባ አጠንከረን መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሌላ በኩል፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚደረገው የ2013 አገራዊ ምርጫ በግል ይወዳደራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ በግል ምክንያት በምርጫው መቀጠል እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ ዛሬ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰራጩት የአጭር የፅሁፍ መልዕክት “ዘንድሮ በሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጅማ ከተማ እንድወክላችሁ ሽማግሌ ከመላክ አንስቶ በተለያዩ መንገዶች እጩ እንድሆን በመጠየቅና ለእጩነት የሚጠበቀውን ፊርማ በራሳችሁ ተነሳሽነት በመፈረምና በማስፈረም የምርጫ ቅስቀሳ እንድጀምር፣ ለቅስቀሳውም «የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ከጎንህ ነን» በማለት ላሳደራችሁብኝ እምነትና አክብሮት ከልብ እያመሰገንኩ፤ በግል እጩነት ተመዘግቤ በነበረው በምርጫው በራሴ የግል ምክንያት ልቀጥል አለመቻሌን ላላሳወቅኳችሁ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ሳሳውቃችሁ ከታላቅ አክብሮት እና ይቅርታ ጋር ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY