ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ልታከናውን በተቃረበችበት ጊዜ፣ ሱዳን አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉ በግድቡ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከፊል ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን አሰተወቀቸ።
ሱዳንና ግብጽ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ አጥብቀው ሲቃወሙ ከመቆየታቸው አንጻር ይህ የአሁኑ የሱዳን ጥሪ፣ አዲስ የአቋም ለውጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ፣ ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ ስምምነቱ የሚፈረመው ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ መናገራቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
በሱዳን በኩል በቅድመ ሁኔታነት የቀረቡት ጉዳዮች፣ በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ሁለተኛ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በኋላም ድርድሩ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ከተሰጠ፣ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት የተደረሰባቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ አገራቱ የመጨረሻ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ እና ድርድሮች የሚካሄዱበት ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ እንዲኖር የሚሉ ሲሆኑ፣ ሱዳን ቀደም ሲል ስታራምደው ከነበረው አቋም በተለየ መልኩ አሁን የአቋም ለውጥ ያሳየችው፣ ቀደም ሲል ሱዳንና ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያደርጉት በነበረው ድርድር ላይ አጥብቀው ሲያነሱ የነበረው ከምንም በፊት በግድቡ ዙሪያ ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ የሚለው አቋም ለድርድሩ ውጤታማ አለመሆን የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳቷ ሳይሆን እንዳልቀረ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ 33ተኛው የምስራቅ ናይል ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ENCOM) ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የምክር ቤቱ (ENCOM) ሰብሳቢን ጨምሮ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የናይል ተፋሰስን በጋራ ማልማት በሚቻልበት መንገድና እስካሁን በተፋሰሱ የተሰሩ ስራዎች ላይ እንደሚያተኩር በተነገረለት በዚህ ስብሰባ፣ የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ግብጽ ሳትገኝ መቅረቷም ታውቋል።