ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በተፈጠረው ሁከት ተጠርጥረውቷ ከነጃዋር መሀመድ ጋር የተከሰሱት ጠባቂዎቹ እነቦና ቲቢሌን፣ ዛሬ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በፕላዝማ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡
“የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ የዋስትና ጥያቄያችንን ውድቅ ማድረጉ አግባብ አይደለም” በማለት 9ኙ ተከሳሾች ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳያቸው ዛሬ የታየ ሲሆን፣ ጠበቃቸው ከድር ቡሎ በችሎት ቀርበው “ተከሳሾቹ በተከሰሱበት የወንጀል አንቀፅ ሰው ከሞተ ከ5 አመት እስከ 20 አመት የሚያስቀጣ መሆኑን በክሱ የተጠቀሰ ቢሆንም የቀረበው ክስ ግን በጥቅል ነው እንጂ እገሌ ተከሳሽ እገሌን ገሏል ተብሎ አልተጠቀሰም ፡
ይህ በሆነበት ሁኔታ የስር ፍርድ ቤት በማስረጃ ተደግፎ መወሰን ነው ያለበት እንጂ ማስረጃ ሳይቀርብ ዋስትና አለመፈቀዱ ተገቢነት የለውም” የሚል የይግባኝ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡
ተከሳሾቹም ካሉበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው በፕላዝማ ባቀረቡት መከራከሪያ “እኛ ምንም ወንጀል አልፈፀምንም። የአቶ ጃዋርን ደህንነት ነው የጠበቅነው፤ በዚህም ልንሸለም ይገባ ነበር፡፡ እኛ አቶ ጃዋርን ደህንነት በመጠበቃችን ታስረናል የጠ/ሚ እና የሌሎች ሚኒስትሮች አጃቢዮች ግን አልታሰሩም በማለት አቤቱታ” አሰምተዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ይግባኝ ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት በይደር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ፣ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ እንዲገደል ተልዕኮ ተቀብላ ሁኔታዎችን አመቻችታለች በሚል የተከሰሰችው ላምሮት ከማል ላይ የስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ማስረጃን ያላገናዘበ እንደሆነ በመግለጽ ዓቃቤ ህግ ያቀረበው ይግባኝ ዛሬ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ታይቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከ2 ወር በፊት ተከሳሿን “በተከሰሰችበት ወንጀል የቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ወንጀሉን ስለመፈፀሟ አያስረዳም” ሲል በነጻ አሰናብቷት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ውሳኔውን ተከትሎ ለጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያለው አቃቤ ህግ ዛሬ በነበረው ችሎት፣ ተከሳሿ ከኦነግ ሸኔ አባል ጋር ሜክሲኮ ተገናኝታ ተልኮ ተቀብላ ሀጫሉን ወደሚገደልበት ቦታ አመቻችታ መውሰዷን የሚገልጽ ማስረጃ እንዳለው ገልጾ፣ “የስር ፍርድ ቤቱ ድርጊቱ የሽብር ወንጀል መሆኑን እያወቀ ተከሳሿን ነጻ ማለቱ አግባብነት የለውም” ብሏል።
የተከሳሿ ጠበቃ በበኩላቸው “የስር ፍርድ ቤት ብይን ተገቢነት ያለው ነው። ማስረጃ ተመዝኖ ነው ብይኑን የሰጠው። ብይኑ ሊነቀፍ አይገባ፤ የቀረበው ምስክር ሟች እንደተገደለ ለምስክሩ ደውላ መናገሯን እና በወቅቱ ቦታውን አላወኩም ብላ በአካባቢው ለነበረ ሰው ስልክ ማገናኘቷን ጠቅሶ በቦታው ስለተገኘች ብቻ ወንጀለኛ ልትባል አይገባም” ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ለተከሳሿ የተለያዩ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ካቀረበ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሀምሌ 5 ቀን 2013 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡