ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የምርጫ ቅስቀሳዎች ዛሬ ሰኔ 9 ይጠናቀቃሉ” በሚል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን የጊዜ ሰሌዳ መነሻ በማድረግ፣ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ደማቅ የማጠቃለያ ምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ውለዋል።
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የሆኑት ፓርቲዎች፣ የመጨረሻ ያሉትን የምረጡኝ ቅስቀሳ በአዲስ አበባና በክልል በተለያዩ መንገዶች ሲያደርጉ የዋሉ ሲሆን፣ የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ ሰልፍ አካሂደው፣ በድጋፉ ሰልፍ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም “የለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመርነውን ስራ ከማሳካት የሚያቆም ኃይል የለም” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይም “ብልፅግናን እንመርጣለን፤ ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና አባላት እና ደጋፊዎች የተሳተፉበት የምርጫ ቅስቀሳ የማጠቃለያ እና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በተጨማሪም ብልጽግና፤ በባህርዳር ከተማ፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ዞን በወልድያ ከተማ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ፣ በሀዋሳና በሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ የማጠቃለያ የድጋፍ ሰልፎችና የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ደማቅ የማጠቃለያ የድጋፍ ቅስቀሳ ያካሄደ ሲሆን፣ የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ “የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ምልከታ እና የምርጫ ዕለት እና ከምርጫ በኋላ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ” በሚል መግለጫ ከመስጠታቸውም ባሻገር “የኢዜማ ሚዛናዊ የከፍታ ጉዞ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ በሚል መርህ” የኢዜማ በራሪ ወረቀት በካራቫን አውሮፕላን ተበትኗል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ደማቅ የምርጫ ዘመቻ ማጠቃለያውን አካሂዷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሀገራዊ ምርጫው ጋር በአንድ ቀን ሊካሄድ እቅድ ተይዞለት የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ተራዝሞ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግባቸው አካባቢዎች አስተዳደሮች ማለትም የከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳደሮች መሆናቸውንና ዞኖች ቅሬታ አቅርበው እንደነበር ጠቅሰው “ብዙ ከመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመፍታት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ምርጫውን እና የሕዝበ ውሳኔውን የግድ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲደረግ ተወስኗል” ብለዋል፡፡