ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዳማ ከተማ በምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘትና የምርጫ ሂደቱን ለማወክ በመሞከር የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ጋልሜቻ አስታውቀዋል።
ስንታየሁ ዑርግዬ የተባለ ግለሰብ፣ በአዳማ ከተማ አባገዳ ክፍለ ከተማ ኦዳ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘቱ በአዋጅ ቁጥር 1177/2011 ዓ.ም የተቀመጠን ክለከላ በመጣስ ወንጀል ተከሶ መቀጣቱን፣ በተመሳሳይ በዚሁ ክፍለ ከተማ በምርጫ ጣቢያ ስድስት ከጠዋቱ 2:40 ላይ ከማል አብዶ የሚባል ግለሰብ፣ ድምፅ ሰጪ መስሎ ድምፅ መስጫ ጣቢያው ድረስ በመግባት ሂደቱን ለማወክ ጥረት በማድረጉ መቀጣቱን ያመለከቱት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ጋልሜቻ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ የተገኘው በአንድ ዓመት እስራትና በ5 ሺህ ብር መቀጣቱን፣ ምርጫውን ለማስተጓጎል የሞከረው ከማል አብዶ የተባለ ግለሰብ ደግሞ በስምንት ወር እስራት መቀጣቱን አስታውቀው፣ ቅጣቱን ያስተላለፈው በምርጫ ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመመልከት የተቋቋመው የአዳማ ወረዳ የወቅታዊ ጉዳይ ችሎት መሆኑንም ተናግረዋል።