ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በየጣቢያዎቹ ይፋ እየሆነ ነው!

ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በየጣቢያዎቹ ይፋ እየሆነ ነው!

ምርጫው በተቋረጠባቸው ከተሞች ዛሬ ድምጽ ሲሰጥ ውሏል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአዲስ አበባ፣ በደብረ ብርሃን፣ በደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር፣ በአብዛዎቹ የኦሮሚያ ከተሞችና እና በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች፣ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በየምርጫ ጣቢያዎቹ ይፋ እየሆነ እንደሚገኝ ታውቋል።

ምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ በተሰጠ በማግስቱ የቆጠራ ውጤታቸውን እንዲያሳውቁ በሚያዘው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ መሰረት እየወጡ ያሉትን ጊዜያዊ ውጤቶች ተከትሎ፣ የምርጫ ክልሎች ደግሞ ከየጣቢያዎቹ ያሰባሰቡትን ጊዜያዊ ውጤት በ5 ቀናት ውስጥ ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የመጨረሻው የአሸናፊዎች ውጤት ማረጋገጫ ደግሞ ምርጫው በተካሄደ በ10 ቀናት ውስጥ በቦርዱ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በትላንትናው እለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሳይጠናቀቅ በቀረባቸው ቦታዎች፣ የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት “በሲዳማ ክልል በሁሉም ምርጫ ክልሎች ከጠዋቱ 5 ሰአት ጀምሮ የድምጽ አሰጣጡ ሂደት የቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለት ይጠናቀቃል። በጋምቤላ ክልል ባሉ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ተቋርጦ የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ በመቀጠል በዛሬው እለት ይጠናቀቃል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁለት ምርጫ ክልሎች ያለው ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ለጊዜው የቆመ ሲሆን ቁሳቁሶች በሙሉ ታሽገው እንዲጠበቁ ቦርዱ ለአስፈጻሚዎች አሳውቋል” ያለው የቦርዱ መግለጫ፣ በዚህም መሰረት ቦርዱ የሚቀጥለው የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታ እና እስካሁን ያለውን ሂደት ገምግሞ የሚደርስበትን ውሳኔ የሚያሳውቅ መሆኑንም ገልጿል።

 

LEAVE A REPLY