ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የተኩስ አቁም መልካም እርምጃ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይና በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር እና ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉት 5 ዲፕሎማቶች የገለጹ ሲሆን፣ ቻይና፣ ኳታር፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፣ ካናዳ እና የአፍሪካ ህብረትም ኢትዮጵያ የወሰደችውን የተኩስ አቁም እርምጃ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ፣ የተኩስ አቁም ሂደቱ ግጭትን ካስቆመና የሰብአዊ ድጋፎች ያለ ገደብ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ ለማድረግ ካስቻለ ውጤታማ እንደሚሆን ገልጾ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ እንዲሁም በትግራይ መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
እንደዚሁም፣ በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር እና ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉት ዴቪድ ሺን፣ ቪኪ ሐድልስተን፣ ፓትሪሺያ ሃስላች፣ ኦውሪሊያ ብራዚሊያ እና ቲቦር ናዥ የተባሉት 5 ታዋቂ ዲኘሎማቶች፣ የተኩስ አቁም ውሳኔውን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል የነበረውን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸው “የፌደራሉ መንግሥት የሰላም አማራጭ ማቅረቡ ትልቅ እፎይታን ፈጥሮልናል” ያሉ ሲሆን “ይህ መልካም አጋጣሚ መታለፍ የለበትም” በማለትም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ እንዲቀበሉ አምባሳደሮቹ አሳስበዋል።
በተያያዘ፣ ቻይና፣ ኳታር፣ ኢምሬትስና የአፍሪካ ህብረት በሰጡት የተናጠል የድጋፍ መግለጫ፣ ተመሳሳይነት ያለው አቋም በማንጸባረቅ በትግራይ ክልል ኢትዮጵያ ያደረገችውን የተኩስ አቁም ጥሪ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ሲቪሎችን ከአደጋ ለመጠበቅ እና ክልሉ ውስጥ ለተጎዱት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የሰብዓዊ እርዳታ ተዋናዮች ደኅንነቱ የተረጋገጠ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ሁሉም ወገኖች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አድርገዋል።
የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኒው እና የአገሪቱ ዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ካርማ ጎልድም ዛሬ በሰጡት የጋራ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ካናዳ እንደምትቀበለው በማስታወቅ፣ ከየትኛውም ወገን ይሁን በትግራይ ክልል በነበረው ቀውስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንምና ሁሉም ወገኖች ይህንን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ እድል በመጠቀም ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት እንዲጠቀሙበት እንዲሁም በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።