ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካ ንብ ተነስተዋል || በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን

ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካ ንብ ተነስተዋል || በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን

በየአቅጣጫው ወደ ማሰልጠኛ ካምፖች እየጎረፈ ያለው ኢትዮጵያዊ ለዓለም አንድ መልዕክት እያስተላለፈ ነው “ኢትዮጵያን አትንኩ” ኢትዮጵያዊነት እንደሚስማር በመቱት ቁጥር እየጠበቀ የሚመጣ፣ ጥልቅ ሚስጢር ያለው ማንነት ነው። ኢትዮጵያን ነክቶ ያላፈረ፣ አጥሯን ተዳፍሮ ያልተዋረደ፣ ወንዟን ተሻግሮ መጥቶ ምሱን ቀምሶ ያልተመለሰ ማን አለ? ኢትዮጵያዊነት መቃብር ሲቆፍሩለት መከራን የሚጠራ ነው ያለው ማን ነበር? በሚጠሏት ሰዎች ለሶስት አስርተ ዓመታት ተቀፍድዳ ተይዛ፣ እንደምሶሶና ማገር ያቆሟትን እሴቶቿን ሲገዘግዝ በነበረ ቡድን መዳፍ ውስጥ ከርማ፣ ልጆቿን በዘርና ጎጥ ሸንሸኖ የጥላቻ ግድግዳ በመሃላቸው ገትሮ ደሟን ሲመጥ በሰነበት አገዛዝ ስር ቆይታ ዘንድሮም ለክብሯ የሚሞትላት ትውልድ ያላጣች ሀገር በእርግጥም ቅኔ ናት ተብላ ብትገለጽ ሲያንስ እንጂ የሚበዛባት አይደለም።

የሰሞኑ ንቅናቄ ኢትዮጵያዊነት ተዳክሟል ብለው ጮቤ ለረገጡም ሆነ ሀዘን ተሰምቷቸው ለቆዘሙት ያልተጠበቀ ክስተት ሆኖባቸዋል። በግሌ በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ቆርጬ ባላውቅም የህወሀት አገዛዝ የቀበረውን መርዝ ለማርከስ ብዙ ዓመታትን የሚጠይቅ የቤት ስራ ይጠብቀናል የሚል ግምት ነበረኝ። ሶስት ትውልዶች ከብሄር ማንነታቸው ወጪ ሀገራዊ ራዕይ እንዳይኖራቸው በትምህርት ፖሊሲ ጭምር ጸረ ኢትዮጵያ ስሜቶች በውስጣቸው ስር እንዲሰድና የጎሪጥ በጠላትነት እንዲተያዩ የተደረገበት የህወሀት የ27ዓመት አገዛዝ በቀላሉ የማይሽር ቁስል፣ በእጭር ጊዜ የማንገላገለው በሽታ ጥሎብን ማለፉን ሳስበው ስለመጪው ጊዜ ነፍሴ በስጋት ትናጥብኛለች። ባለፉት ቀናት ያየሁት ትዕይንት ግምቴን በተወሰነ ደረጃ ስህተት እንደሆነ አረጋግጦልኛል። በስጋት የምትናጠዋም ነፍሴ በመጠኑ እንድትረጋጋ አድርጎልኛል። ኢትዮጵያዊነት አሁንም እንደእቶን እሳት የሚፋጅ ማንነት ሆኖ ለዓለም ተመስክሯል። ስለኢትዮጵያ ውድ ህይወቱን የሚሰጥ ትውልድ በዚህ ዘመንም ተፈጥሯል። ከዚህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን?

የጨለማው ዘመን እድምተኞች በሰሞኑ የኢትዮጵያውያን ዘመቻ ሀገር አድን ንቅናቄ ቅንድባቸው እስኪረግፍ ተበሳጭተዋል። በየሰፈሩ ታጥሯል፣ ከዘሩና ጎጡ አልፎ ስለኢትዮጵያ አንዲት ብልቃጥ ደም የሚያፈስ ትውልድ የለም፣ ኢትዮጵያዊነት ያረጀ ያፈጀ የአንድ መንደር ሰዎች ትርክት ነው ሲሉ የነበሩት ሰሞኑን አንገታችውን ቀብረው መራር እውነታውን እየተጋቱት ይገኛሉ። ከጅማ እስከ ደምቢያ፣ ከምስራቅ ሀረርጌ እስከ ጋምቤላ፣ ከአፋር እስከ ጂንካ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለማዳን ሆ ብለው ሲነሱ በእርግጥም መልዕክቱ እድፍጠው ኢትዮጵያዊነትን ለመቅበር ላሰፈሰፉት ለውጭዎቹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ተላላኪ ሆነው የውክልና ጦርነት ለከፈቱብን የሟሸሸው የህወሀት ቡድን መሪዎችና ለጽንፈኛ ብሄርተኞችም ጭምር ነው። አዎን! ኢትዮጵያን አትንኩ!!!

ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ ሰሞኑን የህወሀት ቡድን ለከፈተብን አስቀያሚ ጦርነት ጥሩና አስተማሪ ምላሽ የሚሰጥ ነው። በህዝብ ማዕበል፣ በህጻናት ደምና አጥንት ድል አደርጋለሁ ብሎ የእልቂት ሰይፉን የመዘዘውን የህወሀት ቡድን በመደበኛው የመከላከያ ሰራዊት ብቻ መግጠም የሚቻል እንዳልሆነ ከወታደራዊ ባለሙያዎች ማብራሪያ መረዳት ይቻላል። ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና የወሰደና ዲሲፒሊን ያለው ሰራዊት እንደጦጣ ዛፍ ለዛፍ ከሚዘል፣ ሰው ጓዳ ገብቶ ሌማት ገልብጦ የተቦካ እህል ሳይቀር ከሚዘርፍ የሽፍታ ሃይል ጋር ውጊያ ማድረጉ የሚያዋጣ አይደለም። የህወሀትን ፍጹም የአረመኔነት ባህሪ የተገለጠበትን ይህን አደገኛ የጦርነት እንቅስቃሴ መግታትም ሆነ ድባቅ መምታት የሚቻለው ተመሳሳይ ቅርጽ ያለው፣ ህዝባዊ ሃይልና በሚሊሺያ የተደራጀ፣ ከመከላከያው በቂ የጀርባ ድጋፍ የሚያገኝ ጠንካራ ሰራዊት በማሰለፍ ነው።

የሰሞኑ ንቅናቄ ከዚህ አንጻር ወቅታዊና ተገቢ እርምጃ እንደሆነ እረዳለሁ። በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ይህን ያህል አስተያየት መስጠት ድፍረት ስለሚሆንብኝ እተወዋለሁ። አንዳንዶች ያለቦታቸውና እውቀታቸው የጦርነት መሀንዲስ እንሁን ብለው በአደባባይ የሚያሰራጩት መረጃና ትንታኔ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚልቅ በመሆኑ የሚሰሙኝ ከሆነ የቄሳርን ለቄሳር እንተው፣ ያለባለቤቱ አይነድም እሳቱ የሚለውን መልዕክቴን ለማድረስ እፈልጋለሁ።

LEAVE A REPLY