ዘመም ይላል እንጂ || በእውቀቱ ስዩም

ዘመም ይላል እንጂ || በእውቀቱ ስዩም

እንደ ጊዜው መክፋት

እንደ ግፉ መስፋት
እንዳገሩ ክስመት
እንዳገሬው ጥመት
እንደሰው ጭካኔ፥እንደ ልቡ ፍሬ
ታምር ነው መትረፍሽ፥ ታምር ነው መኖሬ::

የበጎ ሰው ሀሳብ፥ ሲካድ እለት በእለት
ጉድጓድ ተምሶለት፥ ሰብእና ሲቀበር
በዚህ ዓለም መኖር፥አያስመኝም ነበር ::

ምድሩ ሳር ቅጠሉ፥ በስጋት ተሞልቶ
የማለዳው ሰማይ፥ እንዳንቀልባ ቀልቶ
ታረደ
ነደደ
ከዘብጥያ ወጥቶ
ዘብጥያ ወረደ
የሚል ዜና ብቻ ፥ አየሩን ሲሞላው
ሰው በገዛ ጥላው ፥
በርግጎ ሲሸበር
በዚህ ምድር መኖር፥ አያስመኝም ነበር ፤

አዎ
ለጊዜውም ቢሆን ግፍ ያደነዝዛል
በደል ያስተክዛል
ጊዜም ጠብን ሽሮ፥ ወደ ፊት ይጓዛል
በልብ ሰሌዳ ላይ፤ ቂም ይደበዝዛል
በነገ ያመነ
ልጁን ቀብሮ መጥቶ ፥ ሚስቱን ያስረግዛል ::

ይቅርታና ምህረት
ፍቅርና ህብረት
ከግፍ ጋር ፍልሚያቸው፥ ቢሆን የሞት ሽረት
ዳገት ይወጣሉ፥ በንጥፍጣፊ አቅም
የመኖር ፍላጎት
ዘመም ይላል እንጂ ፥ተገርስሶ አይወድቅም ::

( አዳምኤል )

LEAVE A REPLY