“አሜሪካን እባክሽን ጨዋታ ቀይሪ” || ከመሳይ መኮንን

“አሜሪካን እባክሽን ጨዋታ ቀይሪ” || ከመሳይ መኮንን

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ ወግ መድረክ ላይ የተናገሩት ነገር የፋሲል ደምወዝን አንድ ዘፈን ርዕስ አስታወሰኝ። “ጨዋታ ቀይሪ” የሚለው ዘፈን። ጠ/ሚር አብይ በእሳቸው መረዳትና እውቀት ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ከሀገር እንዲወጡ የተደረገበት፣ የደርግ መንግስት ስልጣን ያበቃበትና፣ ህወሀት ያለ ኮሽታ አዲስ አበባ የገባበት ሁኔታ ምን እንደነበረ የገለጹበትና አሁንም ያንን ተመሳሳይ ታሪክ ለመድገም የሚደረገውን ግርግር የጠቀሱበት ንግግር ይህቺን ጽሁፍ እንድሞጫጭር አደረገኝ። “አሜሪካን እባክሽን ጨዋታ ቀይሪ”

እውነት ለመናገር ጠ/ሚሩ የደርግን የመጨረሻዎቹን ሳምንታት ያስታወሱበት ታሪክ ምንም መዛነፍም ሆነ ስህተት የለውም። ሁሉ ነገር በነጩ ቤተመንግስት ተወስኖ፣ በስቴት ዲፓርትመንት በተጻፈ ስክሪፕት የተፈጸመ ነው። ህወሀት ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር ጀግና ጀግና የሚጫወተው ነገር ሁሌም ያበሳጨኝ ነበር። በአሜሪካን ታዝሎ ቤተመንግስት የገባው ህወሀት ሲፎክርና ሲሸልል በየዓመቱ መስማት እንዴት ያቅለሸልሽ ነበር?! አዎን! የኮ/ል መንግስቱ ከሀገር መውጣት የተቀነባበረ ድራማ ውጤት ነው። እነCNN እና BBC የሽብር ወሬ በማሰራጨት፣ የህወሀት ጦር የማይበገር በአጭር ጊዜ አዲስ አበባን በመዳፉ ለማስገባት የሚከለክለው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ፣ የደርግ መንግስት ውስጣዊ መናወጥ እንደገጠመው፣ ባለስልጣናት ከሀገር ለመውጣት ከውጭ መንግስታት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን፣ በቀን24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀን ፕሮፖጋንዳውን ሲያቀልጡት እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል።

የደርግ ሸንጎ ተረበሸ፣ ባለስልጣናት በድራማው ተጠለፉ፣ የአሜሪካው የስለላ ተቋም CIA ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር እንዲወጡ ያቀናበረው ሴራም ተሳክቶለት ወደሀራሬ ሸኛቸው። በነገራችን ላይ ህወሀት ያለ ጦርነት አዲስ አበባ ገባ የሚለውን ታሪክ ለመለወጥ የህወሀት መሪዎች ሆን ብለው ተኩስ እንዲከፈት አድርገው ምንም በሌለበት 200ሰዎች እንዲገደሉ ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም።
አሜሪካን የደርግ መንግስት እንዲወድቅ ያደረገችበትን ሴራ አሁንም ኢትዮጵያ ላይ ልትደግም ወገቧን ታጥቃ ተነስታለች። ጠ/ሚር አብይ አሜሪካንን በስም ባይጠቅሱም የ1983ቱ መፈንቅለ ድራማ መልኩን ሳይቀይር፣ እንዳለ ኮፒ ተደርጎ ተግባራዊ እንዲሆን ጥረቶች በግልጽ እየታዩ እንደሆነ ገልጸዋል። አሜሪካ ጨዋታውን አልቀየረችም። ትንሽም ቢሆን ሞዲፋይ አላደረገችም። የዚያን ዘመን ተዋናዮች ተቀየሩ እንጂ ሌላው እንዳለ ተገልብጦ ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት ቀን ከሌሊት እየተሰራበት ነው። በአጥንቱ የቀረውና እግር እጁ ተቆርጦ እንደ እባብ እየዳኸ ያለውን ህወሀት አዲስ አበባን ሊይዝ ነው የሚለው ፕሮፖጋንዳ በዚያን ዘመን ሲያስተጋቡት በነበሩት የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች አሁንም በስፋት እየተስተጋባ ነው።

ጠ/ሚሩ እንዳሉትም “አብቅቷል፣ እጅ ስጡ” የሚለው ያን ዘመን በእነኸርማን ኮህን ሲቀርብ የነበረው ጉትጎታ በዚህ ዘመኑ ጄፍሪ ፊልትማን እየተቀነቀነ ነው። ኢትዮጵያ ቀውስ በቀውስ ሆናለች፣ ዲፕሎማቶች ሀገር ለቃችሁ ውጡ፣ ሀገራት ኤምባሲዎቻችሁን ዘግታችሁ ኢትዮጵያን ልቀቁ የሚለው የዚያን ዘመን የአሜሪካ ጫናና ግፊት ዘንድሮም በገንዘብ ድለላ ሀገራትን በማሳመን በስፊው እየተከናወነ ነው።

ኢትዮጵያ ተቀይራለች። የ1983ቷ ኢትዮጵያና የአሁኗ ሰፊ ልዩነት አላቸው። የዚያን ጊዜው ህወሀትና አሁን በእርጅናና በሃጢያት ክምር የሚሰቃየው ህወሀት ልዩነታቸው የሰማይና የምድርን ያህል የሚራራቅ ነው። ያን ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብና አሁን ያለውም እንደዚሁ አንድ ዓይነት የግንዛቤ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ አይደሉም። ሁሉም ነገር ተቀይሯል። ያልተቀየረው የአሜሪካን ጨዋታ ነው። የ1983ቱ በሬ 2014 ላይም እንዲያርስላት ፈልጋ ገብታበታለች። በጩኸትና ግርግር፣ በፕሮፖጋንዳና ሸፍጥ፣ በተንኮልና ሴራ መንግስት ለመገልበጥ እረፍት አጥታ እየባከነች ነው። ህወሀትን በእነCNN ፌክ ወሬ አዝላው ወደአዲስ አበባ ልታስገባው መከራዋን እየበላች ነው። ለእነዛምቢያና ሱዳን ገንዘብ ሸጉጣ ዜጎቻቸውን እንዲያስወጡ ያደረገችው ነገር የዘመኑ ቅሌት ሆኖ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃተ ህሊናው ማደጉ፣ መንግስትም በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አለመሆኑ የአሜሪካንን የሻገተ፣ የተነቃበት ጨዋታ ውጤት እንዳይኖረው አድርጓል። የሚኮበልል መሪ የለም። ሀገር ጥሎ የሚጠፋ ባለስልጣን አይኖርም። በነጩ ቤተመንግስት ፍላጎት የሚለወጥ መንግስት ፈጽሞ አይታሰብም። ኢትዮጵያ አፍጋኒስታን አይደለችም። አዲስ አበባም ካቡል እትሆንም። ታሊባንን ወደካቡል ለማስገባት አፍጋኒስታንን ያመሰችው አሜሪካን በተመሳሳይ ህወሀትን ወደ አዲስ አባባ ለማድረስ ኢትዮጵያን የቀውስ መናሃሪያ ለማድረግ የጀመረችው አሳፋሪ ሴራ በተባበሩት ኢትዮጵያውያን ወኔና ቁርጠኝነት ከሽፎ ለመጪው ትምህርት እንዲሆናት የሚያደርግ ታሪክ በቅርቡ ይጻፋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባኗል። መንግስትም ነቅቷል።

” አሜሪካ፣ እባክሽን ጨዋታ ቀይሪ”

እንበርታ!

LEAVE A REPLY