ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ መቐለ ከተማ አቅንተው ደብረጺዮን ገብረሚካዔልን ጨምሮ ከሌሎች የህወሃት አመራሮች ጋር እንደተወያዩ ተነገረ።
በትላንትናው እለት መቐለ ተገኝተዋል የተባሉት ኦባሳንጆ፣ ከአመራሮቹ ጋር ያደረጉት ውይይት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለመፍታት ወደፊት መደረግ በሚኖርበት ሁኔታ ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ተጠቁሟል።
ኦባሳንጆ ዳግም ወደ መቐለ አቅንተው ከዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ጋር መወያየታቸውን በተመለከተ እስካሁን ከፌዴራል መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሐሙስ ኅዳር 9፣ 2014 ባሰራጨው መረጃ ኦባሳንጆ አዲስ አበባ እንዲሚገኙ በመግለጽ፣ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመገናኘት፣ የሰላም መፍትሔ በማፈላለግ ሂደቱ ዙርያ መወያየታቸውን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን “ከሁለቱም ወገን የማደራደር ጥረቴን አልቀበልም ያለ አካል የለም” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን መናገራቸው ይታወቃል፡፡