ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት 135 የተሰሩ ህገ ወጥ መታወቂያዎችና 173 ሊሰራላቸው የተዘጋጁ ግለሰቦች ፎቶ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።
በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ለህገ ወጥ ተግባራቱ የሚውሉ ኮምፒዩተር፣ የህትመት ማሽን እና የተቀረጹ ማህተሞች በስራ ላይ ባለበት እጅ ከፍንጅ ተይዟል ተብሏል።
በተመሳሳይ በእዚሁ ክፍለ ከተማ የወሳኝ ኩነት ባለሙያ የሆነ ግለሰብ መታወቂያ ሲሸጥ ተደርሶበት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በማህበራዊ ገጹ አስፍሯል።
ጊዜያዊ መታወቂያ የሚሰጥበት አሰራር ከህዳር 6 እስከ 15 እንደሚቆይ ይታወቃል። በሌላ በኩል ከአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ጋር ተያይዞ ሕገ-ወጥና ተመሳስሎ የተሰራ መታወቂያ እንዲሁም መታወቂያ ለማይገባው ሰው መታወቂያ የሰጠ ግለሰብ ወይም አካል ከ3 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል መባሉ ይታወሳል።