ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአማራ ክልል በተለይም በጦርነት ቀጠና ውስጥ በሚገኙ 5 ዞኖች ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን ሰብል በቂ እንክብካቤ በማጣት ምክንያት መታጣቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ ይህንንም ጉድለት ለማካካስ የፀጥታ ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ሲሰሩ ከነበረው በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
እየተተገበረ ባለው የመፍትሄ ስራም እስከ አሁን ድረስ አጨዳ ከደረሰባቸው አካባቢዎች ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚሆን ሰብል በመሰብሰብ ከ74 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሚሆን ሰብል ለመሰብሰብ መቻሉን እና ይህም ከመሬት ሽፋን አንፃር ወደ 26 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው መሬት ምርቱ መሰብሰብ መቻሉን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
አክለውም የምርት አሰባሰብ ሂደቱ በዋናነት በሰው ጉልበት እንደሚከናወን በማውሳት ይሄንንም ለመቀየር 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ኮምባይነሮች ወደ ሥራ ገብተው የምርት አሰባሰብ ዘዴው በፍጥነት እያገዙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።