ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አሜሪካ የተመለሱት የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የአሜሪካ መንግሥት ለሕወሓት ይወግናል መባሉን ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
አክለውም በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መገናኘታቸውን ሲገልፁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት በሰኔ ወር 2013 ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም እና በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በአግባቡ እውቅና አለመስጠቷን በማውሳት ቅሬታቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት የህወሃት ቡድን በወረራ የያዟቸው የአማራ እና አፋር አከባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ መሆኑን ነግረውኛል ብለዋል፡፡ በተቃራኒው የህወሃት መሪዎች ፍላጎት ደግሞ ተቋርጧል ያሉትን የሰብአዊ አቅርቦት ማስከፈት መሆኑን መስማታቸውንም ፌልትማን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የሁለቱም አካላት አላማ ፖለቲካዊ ፍላጎት ካለ በስምምነት ሊሳካ እንደሚችል በመግለፅ “ነገር ግን የፌዴራል መንግስትም ሆነ ህወሃት ወታደራዊ አማራጮችን መቀጠላቸው አስጊ ነው” ብለዋል
የአሜሪካ ላለፉት በርካታ ወራቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ስታሳርፍ የቆየች ሲሆን ዜጎቷ አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ከመወትወት አንስቶ ጉዳዩን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ በመውሰድ ውሳኔ እንዲሰጥበት በትኩረት ስትሠራ እንደነበር ይታወቃል።