ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት ለግሉ ዘርፍ፣ ለግብርና ግብዓትና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ።
መንግስት አስቀምጦት የነበረው የብድር ክልከላ መነሳት የአገሪቷን ምጣኔሃብት ለማነቃቃት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ተነግሯል።
የምጣኔሃብት አሻጥሮችና የጥቁር ገበያውን መቆጣጠር እንዲቻል የግል እና የመንግስት ባንኮች የሚሰጡትን ብድር በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ ተደርጎ እንደነበረ ይታወቃል።
ይሁንና ለ3 ወራት ተጥሎ የቆየው ክልከላ መነሳቱ ምጣኔሃብቱን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለፀው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድርና ሃብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉነህ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት ባንኩ በዚህ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ተዘጋጅቷል።
ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር ለግሉ ዘርፍ፣ 30 ቢሊዮን ብር ለግብርና ግብዓት ሲሆን ቀሪው ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደሚውል አብራርተዋል።