የሃገራችን ፖለቲካ አድሮ ቃሪያነት መገለጫው ብዙ ነው || መስከረም አበራ

የሃገራችን ፖለቲካ አድሮ ቃሪያነት መገለጫው ብዙ ነው || መስከረም አበራ

ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በተመለከተ እየሄድን ያለበት አንድ እርምጃ ወደ ፊት አምስት እርምጃ ወደ ኋላ የሆነ አካሄድ አዙሮ አዙሮ እዛው የተነሳንበት ቦታ የሚያንፏቅቀን አባዜያችን ነው።

በዚህ ረገድ ተወቃሹ መንግስት ብቻ አይደለም። ይልቅስ በህወሃት ዘመን ለፍትሃዊነት በመሟገት የምናውቃቸው ሰዎች ዛሬ “እከሌን የማታስሩት እስከመቼ ነው” እያሉ የእስር ትዕዛዝ መዘርዝር ለመንግስት የሚያቀብሉ የእስር “Commentators” ሆነው ቁጭ ብለዋል።ጭራሽ “እከሌን ባላሳስር እኔ አይደለሁም” እየተባለ ሲፎክር በሰው ሳይሆን በራሴ ደርሶ ጆሮዬ ሰምቷል።

ይህን የሰማሁ ዕለት የመንግስት አዝማሪ መሆን ይህን ያህል ክፉ እና እብሪተኛ ካደረገ አጋጣሚውን አግኝቶ መንግስት የሆነውማ የተሻለ ክፉ ነው ማለት ነው አስብሎኛል። እኔ በጣም የማዝነው በእነዚህ ወገኖች ነው እንጅ ከኢህአዴግ ውስጥ ህወሃት ስለተወገደ የሚፈለገው ነፃነት እና እኩልነት እንደማይመጣ ከተገነዘብኩ ሰነባብቻለሁ።

በህወሃት ዘመን ነፃነትን ፈልጎ ይታገል የነበረው ጎራ ቋንቋው መደበላለቁ ድሮም በቋፍ የነበረውን መንግስት የፈለገውን እንደ ጥጃ እየጎተተ እንዲያስር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የባሰው ሲመጣ ደግሞ ለፍትህ ያለ ፍርሃት የሚሞግትን ሰው “እከሌ መታሰር ፈልጓል ግን የሚያስረው ጠፋ” ሲባል እሰማለሁ። እስርን ሞምባሳ ሄዶ እንደመዝናናት የሚያስቆጥር ምን አይነት የአስተሳሰብ ምክነት እንደገጠመን ግራ ይገባኛል! እንዴት ያለ ራስን መናቅ ነው ሰው እስር ቤት በመግባቱ በሚያገኘው ዝና ተጠቃሚ ይሆናል የሚል እሳቤን የሚያመጣው? ሰው በነፃነት ከኖረ (ዝና ፈላጊ ከሆነም) ለሃገር ለወገን ጠቃሚ ነገር ሰርቶ እስር ቤት የሚሰብረውን ሰብዕናውን ሳያጣ ዝና ማጎኘት እንደሚችል ማሰብ ከባድ ሆኗል። እስር ቤት የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ቀውስ በአንድ ሳምንት ከሚረሳ ታስሮ የሚገኝ ዝና ጋር ማወዳደር ከድሮ እስከ ዘንድሮ ብቅ ያሉ የመንግስት አዝማሪዎች የጭካኔ ጥግ ነው።

የመንግስት አዝማሪነት ትልቅ ማዕረግ መስሎት ለፖለቲካችን መቃናት በገባቸው ልክ የሚታገሉ ሰዎች ይታሰሩ እያለ የሚጎተጉት ሁሉ ጌታ የተቀየረ ዕለት እጣ ፋንታው ምን እንደሚሆን የትናንቶቹን ባለ ጊዜ ነን ባዮች ማየት ነው።

ጌታ ተቀይሮም ፖለቲካው ባለመቀየሩ ትግላቸውን የቀጠሉ ጥቂቶች ግን እውነተኛዋን ነፃነት ናፋቂዎች ናቸውና እንግልታቸውም ቀጣይ ነው። እያየን ያለነው ይሄንኑ ነው። ታምራት ነገራ የተቀየረውን ጌታ ኦህዴድን ፖለቲካ አብጠርጥሮ የሚያውቅና ያለፍርሃት የሚተች ነው። ይሄው መርገም ሆኖ ተቆጥሮ እስር ቤት እንደሚከተው ግልፅ ነበረ። አሁን ታሜን እስር ቤት የወረወረው ተረኛው አሳሪ በምን ምክንያት እንዳሰረው ባያሳውቅም ነገሩ ከዚህ እንደማያልፍ ግልፅ ነው።

ታምራት ነገራ የሚታሰር ሳይሆን የሚደመጥ ተንታኝ ነበር። ከዓለም አቀፍ እስከ አህጉር አቀፍ ጅኦፖለቲካዊ ነገሮችን የሚረዳበት፣ተረድቶም የሚገልፅበት መንገድ ድንቅ ነው። የሃገራችንን ፖለቲካ በአጠቃላይ በጥልቅ የሚረዳበት መንገድ ሁሉም ቦታ የሚገኝ አይደለም።የኦህዴድ/ብልፅግናን ፖለቲካ ውስብስቦሽ መረዳቱ፣ያለፍርሃት መተቸቱ ደግሞ መንግስትን እና አዝማሪዎቹን ማስደንገጡ አልቀረም። አምባገነን ሲደነግጥ ደግሞ ያስራል! ታሜ ላይ የሆነው ይሄው አሰልች የአምባገነኖች ዘይቤ ነው።

LEAVE A REPLY