ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሽፋን በማድረግ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉ አራት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፌደራል ፖሊስ አባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ህገወጥ እስር በመፈፀምና በማስገደድ ሁለት መቶ ስልሳ ሺህ ብር የተቀበሉ መሆኑ ተገልጿል።
ተከሳሾቹ ምርመራ የማከናወንና ተጠርጣሪ የመያዝ የሥራ ድርሻ ሳይኖራቸውና ምንም አይነት ትዕዛዝ ሳይሰጣቸው የግል ተበዳይን በወቅታዊ ጉዳይ ትፈለጋለህ በማለት በስራ ተሽከርካሪ አሳፍረው 1 ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው ጠይቀው 260 ሺ ብር ወደ አንደኛው ተከሳሽ የቁጠባ ሂሳብ እንዲያስገባ በማድረግ ተከፋፍለዋል ተብሏል።
በመሆኑም በ1996 ዓ/ም የወጣዉን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀፅ 9(2) ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል።
ዛሬ ታህሳስ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል።