በወራሪው የጠላት ሃይል ቁጥጥር ስር የነበሩ አከባቢዎችን ነፃ የማውጣት እርምጃን ተከትሎ የወልዲያ ከተማ እና አከባቢው መንግስት በወሰደው ጠንካራ የማጥቃት እርምጃ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣት በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን።
ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ እና አፋር ክልል ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ላደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ እና አኩሪ ተጋድሎ ከልብ እናመሰግናችኋለን፤ እናከብራችኋለን።
ለዚህ ታሪካዊ የድል ምዕራፍ ስላበቃችሁን ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ።
አሁንም የድል ግለቱን ጠብቆ በወራሪው የጠላት ሃይል ቁጥጥር ስር ያሉ ቀሪ ጥቂት አካባቢዎችን በአጭር ጊዜ ነፃ የማውጣት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ሃገራችን ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና እንዳትላቀቅ ብሎም የከፋ ጫና ውስጥ እንድትወድቅ ከውስጥ እና ከውጭ ያሉ ሃይሎች ተባብረው እየሰሩ መሆናቸው በግልፅ ይታወቃል።
እነዚህ ለጥፋት ያበሩ ሃይሎች የኢትዮጵያን ውድቀት ለማብሰር ሁሉንም ምድራዊ የጥፋት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉ በገሃድ በሚፈፅሙት ጫና እና ሴራ መረዳት ይቻላል።
ይሁንና ኢትዮጵያዊነት የነሱን የጥፋት ድግስ ታግሶ ለማስተናገድ የሚፈቅድ የሞራል ስብራት እንደሌለው በየጊዜው የሚያስመዘግባቸው አኩሪ ድሎች በቂ ማሳያ ናቸው።
በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ ክፍለ አለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ”No More” አለም ዓቀፍ ንቅናቄ በተሰለፋችሁበት መድረኮች ለምታደርጉት ተጋድሎ ከልብ እናመሰግናለን።
የውጪውን ግንባር በደማቅ ኢትዮጵያዊ አንድነት እና ህብረት ለምታደርጉት ሁሉአቀፍ ርብርብ እና ትርጉም~አዘል ጫና ልዩ አክብሮታችን እና አድናቆታችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ።
ሁሉም ለጥፋት ግንባር ፈጥረው ይባክናሉ፤ ይሁንና በጠንካራ የአንድነት መንፈስ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዳር እስከዳር አኩሪ ድሎች እያስመዘገብን ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥላለን።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን