I mean it seriously!
ወሎ ጦርነቱን ተሸክሞ መቆየቱን መካድ አይቻልም። ጦርነቱ ተጭኖበታል ስንል ደግሞ for tactical reason ሊሆን ይችላል ከሚል ግምት በመነሳት ነው። ከዚህ ውጭ፣ ፖለቲካዊ ሴራና ወታደራዊ አሻጥር (political conspiracy and military sabotage) ተፈፅሟል የሚለውን ክስ ዱሮም አልተጋራንም። ከመሬት ተነስተን ማንንም የመክሰስ/የመወንጀል ልምድና ማህበራዊ ስሪት የለንም። ተጨባጭ ማስረጃ ሲኖር ግን፣ በይፋ ለመናገር የማናመነታ፣ የግልፅ ማህበረሰብና ባህል (open society and culture) ውጤቶች ነን። የወጣንበት ማህበረሰብ ከመንጋነት ይልቅ ምክንያታዊነት የሚያጠቃው ስለመሆኑ ማስረዳት አይጠበቅብንም።
በነገራችን ላይ፣ በቁርጡ ቀን ከጎናችን ለቆሙ ሁሉ ያልተቆጠበ፣ ልባዊ ምስጋናችንን ስንገልፅ ባጅተናል። ከምንም በላይ ውድ ህይወታቸውን፣ እንዲሁም አካላቸውን የሰጡ ወንድም-እህቶቻችንን ውለታ ለመክፈል ይቅርና፣ ለመግለፅም እንደሚከብድ ደጋግመን ገልፀናል። ከዚያም በመለስ በገንዘብና ቁሳቁስ የደገፉንን ሁሉ በእጅጉ አመስግነናል። ያለፉ posቶቻችንን መለስ ብሎ ማዬት ይቻላል። በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ትናንት የተደረገልንን የምንዘነጋና/የምንረሳ፣ ውለታ ቢሶች አይደለንም።
ይህም ሆኖ፣ ጦርነቱን ተሸክመን መቆዬታችን ሊደበቅ የማይችል ሐቅ ነው። የወሎ ህዝብ ከቆቦ አንስቶ – ወልዲያ፣ መርሳ፣ ውጫሌ፣ ቢስቲማ፣ ሐይቅ፣ ሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ጋሸና፣ መቄት፣ ደብረዘቢጥ፣ ወገልጤና፣ ዳውንት … ያደረገውን መከላከልና የጀግንነት ተጋድሎ እንዴት ይሆን መግለፅ የሚቻለው? የትግራዩ ወራሪ ኃይል ወደ ደሴ ዙሪያ ከተጠጋ በኋላ፣ በተለይ አላሻ ሜዳና ቦሩ-ስላሴ ላይ ስለተደረገው ከባድ ውጊያስ እንዴት ሊዘገብ ይቻል ይሆን? የትግራዩ ወራሪ ኃይል ካሰለፈው ጠቅላላ ተዋጊ ኃይሉ፣ እስከ80% (ሰማንያ በመቶ) የሚገመተው ያለቀበት፣ በወሎ ግንባር መሆኑ እየተነገረ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው፣ ወታደራዊ መሪዎቻቸው፣ በተለይ ደሴን መቆጣጠር ከቻልን፣ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ አዲስ አበባ መግባት እንችላለን የሚል ስሌት ስለነበራቸው ነው። ለዚህም ነው፣ እነጀኔራል ፃድቃን፣ ደሴ ከተያዘች በኋላ፣ “ጦርነቱ ተጠናቅቋል” በማለት ተኩራርተው የተናገሩት። እንዳሉትም፣ በአጭር ጊዜ ተንደርድረው ወደ ደብረ-ብርሃን ከተጠጉ በኋላ፣ የጦርነቱን ውጤት ስለቀየረው ምስጢር በሌላ ርዕስ ሥር ልንነጋገርበት እንችላለን።
ወደተነሳንበት ርዕስ ስንመለስም፣ ወሎ ጦርነቱን ተሸክሞና/ተጭኖበት ስለመቆየቱ በርካታ ማሳያዎችን (በሌላ ጽሁፍ) ማቅረብ ይቻላል። ጦርነትን ለወራት ተሸክሞ መቆዬት አንደምታው ሰፊ ነው። ስለህነም፣ የወሎ ህዝብ በምንምና በቀላሉ ሊተመን የማይችል (incalculable) ከፍተኛ ጉዳትና ኪሣራ ደርሶበታል። ኪሣራው በንብረት ዘረፋና ውድመት ብቻ የሚገለፅ አይደለም። ከቁሳዊ ጉዳቱ በላይ፣ ሰብኣዊ እልቂቱ እጅግ ዘግናኝና ከውስጣችን የማይጠፋ ጥልቅ ሀዘን የፈጠረ ነው። የወሎ ፋኖ መሪዎች የነበሩትን፣ እነመሐመድ ቢሆነኝንና እነሞላ ደስዬን ጨምሮ፣ በርካታ ጀግኖቻችንን አጥተናል።
ጀግኖቹ በክብር ቢወድቁም፣ እነምሬ ወዳጆ የወሎ ፋኖን ትግል እየመሩ፣ የወራሪው ኃይል ግብኣተ-መሬት የሚረጋገጠው በወሎ ምድር መሆኑን በድላቸው አውጀዋል። በርግጥ ስለወሎ ፋኖ የጀግንነት ውሎና ተጋድሎ ብዙ/በበቂ ሁኔታ አልተዘገበም። ከዚሁ ጋር፣ በተለምዶ “ሽርጣሞቹ” ተብለው የሚገለፁት፣ እነሀሰን ከረሙና እነሻለቃ ሹመት የሱፍ ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎ ገና በዝርዝርና በወጉ አልተገለፀም። በምዕራብ ወሎ፣ በኮምቦልቻና በደሴ ዙሪያ የተፈጠሩ የተለያዩ አደረጃጀቶችና የተደረጉ ተጋድሎዎችም፣ ገና በአግባቡ አልተነገረላቸውም።
በዚህ ፈታኝ ሁኔታ፣ ወሎን “በፈርጣጭነት …” የሚፈርጁና፣ በደረሰብን ፈርጀ-ብዙ ጉዳትና ኪሳራ ለመሳለቅ የሚቃጣቸውን ወገኖች፣ ከዋናው ጠላት ለይተን አናያቸውም። የወሎ ህዝብ ፈሪም – ፈርጣጭም አይደለም። ህዝቡማ በወልዲያ፣ በደሴና በሌሎችም ግንባሮች፣ የወገን ጦር እስከሚያፈገፍግ ድረስ፣ ስንቅ ከማዘጋጀትና ከማቅረብ ባለፈ፣ በአውደ-ውጊያው በመገኘት ጭምር፣ ተተኳሾችን/ጥይቶችን በማቀበል፣ ቁስለኛን በማንሳት፣ ተዋጊውን ኃይል በማበረታታትና ሞራል በመስጠት ያደረገው ተሳትፎና ያሳየው ጀግንነት፣ የታሪክ ምስክርነትን የሚማፀን እውነት ነው።
የወገን ጦር ሲያፈገፍግ ግን፣ ታንክ፣ ቢ.ኤም፣ ሞርታር፣ ዲሽቃ፣ ብሬን፣ ስናይፐር፣ ክላሽንኮፕ … የታጠቀን ኃይል፣ ህዝቡ በባዶ እጁ እንዴት ነበር ሊከላከል የሚችለው? በዘመናዊ መንገድ የተደራጀው፣ በሚገባ የታጠቀውና የዳበረ የውጊያ ቴክኒክ ያለው ጦር ያልቻለውን፣ ተርታው ህዝብ እንዴት ነበር በደም ሰክሮ የሚመጣን ወራሪ ኃይል ሊመክት የሚችለው? እኛስ ብንሆን ወራሪውን ኃይል ጭራቅ አድርገን በመሳል ስናስፈራራ ቆይተን፣ ህዝቡ በቤቱ ቁጭ ብሎ እንዲቀበለው ነበር የምንጠብቀው? የወሎ ህዝብ፣ ከወገን ጦር ጋር ከማፈግፈግ ሌላ፣ ምን አማራጭ ነበረው? ወደኋላ ተመልሶ፣ አካባቢውን ከወራሪው ኃይል ነፃ ለማውጣትስ የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎለታል? ከመጀመሪያውስ ወሎ በአግባቡ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ፍላጎት ነበር? ይህም ሆኖ፣ በርካታ ወጣቶች፣ የወሎ ፋኖን በመቀላቀል፣ ወራሪውን ኃይል አልተፋለሙም? ከሌሎች የመንግሥት ኃይሎች ጋር በመሆንስ፣ አካባቢያቸውን ከወራሪው ኃይል ነፃ አላወጡም?
ያገጠጠው እውነት ይኸ ሁኖ ሳለ፣ የተፈጠረውን ፈታኝ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የወሎን ክብር ለማዋረድና፣ በደረሰብን ጉዳት ለመሳለቅ የምትሞክሩት እናንተ እነማናችሁ? I mean it seriously!