ዝምተኛው ዳያስፖራ አንበሳ ሆኖ ተነሳ! || ሰማነህ ታምራት ጀመረ – ኦታዋ ካናድ

ዝምተኛው ዳያስፖራ አንበሳ ሆኖ ተነሳ! || ሰማነህ ታምራት ጀመረ – ኦታዋ ካናድ

እግዚአብሔር ዓዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ከእንስሳት ለይቶ የማስተዋል፤ የማሰብና በአግባቡ የመምራት ክህሎት ሰጦ በምድር ላይ አንግሶታል። ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ሲል ቀደሰው። ኢትዮጵያንም የሰው ዘር መገኛ አርጎ ፈጠራት። በግዮን ወንዝ ተከባ የምትገኘውን ቅድስት ሃገር በቅዱስ መጽሃፉ ከአርባ ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን አወድሷል። ዘሯም በዓለም ዙሪያ እንዲበዛ ፈቅዷል።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን በዓለም ዳርቻ ሁሉ እንደ አሽዋ ተበትነው፤ እንደ ፅጌረዳ ፈክተው፤ በቀስተ ደመና ደምቀው፤ እንደ እንጉዳይ በዝተው በዓለም ዙሪያ የሚገኙት። በየሄዱበትና በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ ጨዋነትን ከነስብእናው፤ ትህትናን ከነግብረገብነቱ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ከነቅድስናው፤ እውቀትን ከነአስተዋይነቱና ከነስነምግባሩ ይኖሩታል።

በጨዋነታቸውና በመልካም ግብረገብነታቸው ምክንያት አንዳንድ ሃገራትና ሃገር ከሃዲዎች የኢትዮጵያዊያንን ትእግስት እንደ ፍርሃት፤ መልካም ስነምግባራቸውን እንደ አጎብዳጅነት ሲቆጥሩት ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲጦዝ አገሬን አትንኩብኝ የሚል በአንድ ወገን በሌላው በኩል ዓይኑን ጨፍኖ ጆሮው ላይ ተኝቶ የነበረው ዳያስፖራ በንዴትና በቁጭት ማንነቱንና አገር ወዳድነቱን ዓለም ጉድ እስኪል እያሳየ ነው። ዳያስፖራው ትዕግስት፤ አስተዋይነትና ረግታን ተላብሶ ነገሮችን በማቻቻል ሲአስተውል አርባ ዓመት አስቆጥሯል። ይህን የኢትዮጵያዊያንን ቻይነትና የማስተዋል ስነምግባር ያልተረዱ የፖለቲካ አቀንቃኞች ጭንቅላቷን በአሽዋ ውስጥ እንደደበቀች ዔሊ አስመስለው ሲአጣጥሉትና ሲሳለቁበት አንዳንዴም በጥርጣሬ ዓይን እየማተሩ በአድርባይነት፤ በፈሪነት ወዘተ ሲፈርጁት ቆይተዋል።

ዛሬ ይህ ሃይል ሃገሩ በውስጥ አጥፊዎችና ክሃዲዎች ለድርድር ስትቀርብ፤ በኢትዮጵያ እውቅ ጠላቶች ስትጠቃ፤ ስትደፈርና ስትንገላታ ሃይማኖት ሳይገድበው፤ እራስ ወዳድነት ሳያሸንፈው ዝምታውን ሰብሮ ከተኛበት ዓለም ወጦ ሃገሩን ለመታደግ ሆ! ብሎ ተነስቷል። አይዞሽ ሃገሬ እኛ እያለን አትደፈሪም እያለ ለሃገሩ አለኝታነቱን በገቢር ገልጿል።

በዓለም አድባባይ ሰልፍ ወጥቶ ኢትዮጵያን የነካ የለውም በረካ እያለ በየአሃጉሩ የተመመበት ብዙ ይናገራል። በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መከበር ሰበብ፤ በውሸት ፕሮፖጋንዳ ታጅበው ሃገሩን ሊበትኑና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊአንበረክኩ የተነሱትን ሃያል ሃገራትና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በቃቻሁ (# NO MORE) እያለ በገሃድ መገዳደር ጀምሯል። ለሃገሩም ዝብ ቆሟል።

ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ከአዎርፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ፤ ከአውስትራሊያ እስከ አስያ ድምፁን ጎላ፤ አንገቱን ቀና፤ ባንዲራውን ከፍ፤ አለቃውንና መሪውን በክብር አቅፎና ደግፎ አትንኩን የአድዋ ልጆች ነን ሲል ዓለምን ያለመሳሪያ አንቀጥቅጧል።

በሃብት ተመክተው ሊአንበረክኩን የሞከሩ ሃያል ሃገራትን ሃብታችሁ ይቅርብን እንጂ ክብራችንና ኩራታችንን፤ አይበገሬነታችንን ልትነኩብን አይገብም ሲል መልእክቱን አስተላልፏል። እውነት ሰብዓዊነት የተላበሳችሁ ሃገራትና ሕዝቦች ከሆናችሁ ሃገሬን እወዳለሁ ያለን ሕዝብ ልታዝኑለት፤ ልትረዱትና ልትንከባከቡት ይገባችሗል እንጂ ሰብዓዊ ክብሩን፤ ሕዝባዊና ሃገራዊ ኩራቱን በማስፈራራት ልትወስዱበት አይገባችሁም ሲል ድምፁን አሰምቷል።

ከሰልፉ ባሻገር በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ልዩ ልዩ የእርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ፤ የቁሳቁስና የሙያ ማሰባሰብ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል። በቶሮንቶ፤ አልበርታ፤ ዋሽንግተን፤ ሎሳ አንጀለስ፤ ሌባኖን፤ ብራሰልስ፤ ስዊስ፤ ቫንኩቨር፤ ኦታዋ፤ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ አሸልቧል እየተባለ ይታማ የነበረው ብዙሃኑ (silent majority) ዳያስፖራ በነቂስ ወጦቶ በብዙ ሽህ የሚቆጠር ዶላር ( ብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር) የማሰባሰቡን ተግባር በሰፊው፤ በፍላጎትና በቁጭት ተያይዞታል። በእርዳታ ስም ሃገሩን ቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ የቋመጡትን ባንዳዎችና የውጪ ጠላቶቹን ቅስም ሰብሯል። በተለይ ሃያላን ሃገራት እርዳታችሁን በጉያችሁ ይዛችሁ አትምጡብን ብሏል።

ብዙሃኑ ዳያስፖራ በራስ መተማመን ስነምግባር የታነፀች እትዮጵያን መልሶ ለማቋቋም ቃል ገብቷል። ያሸለበው ዳያስፖራ ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ!!ብሎ ተነስቷል። በዝምታና በትዕግስት ተሸብቦ የነበረው ደግሞ ሲአገሳ ከፊቱ የሚቆም ወንበዴና ሃገር ሻጭ አይኖርም። ከሰሞኑ የሚስተዋለው የኢትዮጵያዊነት ሃይልና የዳያስፖራ አትንኩን ባይነት ወኔ ከቆፎው ወጥቷል። ከዚህ በኋላ የሚአቆመውም ሆነ የሚገዳደረው ምድራዊ ሃይል አይኖርም።

በመጪው ጃንዋሪ 2022 ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዳያስፖራ መሪው ባደረጉለት ጥሪ መሰረት ሃገሩ ሄዶ ኢትዮጵያን፤ ዘመዶቹንና ወገኑን ይጎበኛል። ተጨባጩን ሁኔታ አይቶ ይመለሳል። በዚህ ወደ ሃገር ግቡ እንቀስቃሴ (great home coming) ሃገሪቱ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደምትሆን ይገመታል።

በግርድፉ ከትኬት ሽያጭ US$1.1 ቢሊዮን ዶላር፤ ዳያስፖራው ከሚአስገባው ቁሳቁስ ወደ US$300 ሚሊዮን ዶላር፣ ለዘመዱ የሚሰጠው ድጎማና ለአንድ ወር መቆያ ወጪ ከሚአደርገው US$1.5 ቢሊዮን ዶላር፤ እያንዳንዱ ዳያስፖራ ቦሌ ሲገባ ሙዳየ እርዳታ ሳጥን (ካሳ ፎርቶ) US$100 ቢከት US$100 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቱሪስት ቪዛ ክፍያ በንፍስ ወከፍ $50 ቢከፍል US$50 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል። በጥቅሉ ከዚህ ወደ እናት ሃገር የመመለስ ተንሳሽነት ኢትዮጵያ ከUS$ 4.5-US$ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ልታገኛ ያስችላታል። ይህ ደግሞ አሜሪካ በዓመት የምትሰጠውን እርዳታ በአራት እጥፍ ይሆናል። እራስን መቻል ከዚህ በላይ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል። እሰይ ዳያስፖራ በያላችሁበት ኑሩልኝ፤ ክበሩልኝ ትላለች ኢትዮጵያ።

ከጥር 2014 ጀምሮ ዳያስፖራው ተመልከት ባንዲራህን፤ እይ ዓላማህን፤ ተከተል መሪህን እያለ ወደ እናት ሃገር ኢትዮጵያ ይተማል። አንበሳው እንደ ቀደምት አያቶቹ፤ ቲዎድሮስ፤ ምኒሊክ፤ አሉላ፤ አቢቹ እያገሳና ታሪክ እየሰራ ሃገሩን ያሻግራል። ዳያስፖራው አንበሳ ሆኖ ስለተነሳ እጅ ለእጅ ተያይዞ ይሆናል ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ እያለ የዘመቻ ከበሮ መጎሰም ጀምሯል። ኢትዮጵያም እጇን ዘርግታ እንኳን ደህና መጣችሁ ግቡ ብና ጠጡ ልትል ተዘጋጅታ ትጠብቃለች። መልካም የፈረንጆች ገና እና አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ ሃገራችሁ ትመኛለች።

መልካም ጉዞ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር፤

LEAVE A REPLY