ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ብቻ ወደ 1.3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የግልና የመንግስት ንብረት ማውደሙ ተገለፀ፡፡
የዞን አስተዳዳሪ ሰለሞን ታምሩ እንደገለፁት አሸባሪው የሸኔ ቡድን በተንቀሳቀሰባቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ገልጿል፡፡
ቡድኑ ባለፉት 2 ዓመታት አርሶ አደሮችን ምግብ አምጡ እያለ ሲያስገድድ የነበረ ሲሆን ለእኩይ ዓላማው ባልተባበሩ የዞኑ ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ሲፈፅም እንደነበረ ገልፀዋል።
የመንግስት ሰራተኞችን፣ ኢንቨስተሮችን፣ ተቋራጮችን፣ ያለ ክፍያ የሚሰሩ ሚሊሻዎችን፣ አርሶ አደሮችን እና የሃይማኖት አባቶችን ኢላማ ያደረገ አሰቃቂ ግድያ መፈፀሙንም ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ወደ 790 የሚደርሱ የዞኑ ነዋሪዎች በአሸባሪው ሸኔ አሰቃቂ ግድያ የተፈፀመባቸው ሲሆን ከዚህ ወስጥ ወደ 301 የሚሆኑት አርሶ አደሮች መሆናቸው ቡድኑ ፀረ-ሕዝብ መሆኑን ያሳየበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም ቡድኑ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በመሆን ኦሮሚያን፤ አልፎም ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ያነሱት የዞኑ አስተዳዳሪ ሰለሞን ታምሩ በዚህም ወደ 1.3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የግልና የመንስት ሀብት አውድሟል ብለዋል፡፡
በዞኑ ከሚገኙ 452 የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ማለትም ወደ 226 የሚደርሱ የቀበሌ አስተዳደሮችን ሙሉ በሙሉ ዘርፎ፤ አይጠቅመኝም ያለውን አቃጥሎና አውድሞ መፈርጠጡን ነው የገለፁት።