ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካ መንግሥት በእኛ ጉዳይ ከሌሎች አገራት ጋር ሳይሆን ከእኛ ጋር መወያየት አለበት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
ዛሬ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከመወያየት ይልቅ በተደጋጋሚ ከሌሎች አገራት ጋር መነጋገርን መርጣለች ብለዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወያየት ከፈለገች እኛ ሁሌም ዝግጁ ነን፤ በእኛ ጉዳይ ላይ ከእኛ ጋር መወያየት አለባት ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የተጠናቀቀው የፈረንጆች 2021 ዓመት ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተነዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት አገሪቱ ትፈርሳለች ብለው የተለያየ አቋም የያዙ አገራት እና ተቋማት የታዩበት ዓመት እንደነበር አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አስታዉቀዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ወደግብፅ፣ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢምሬት በማቅናት መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ከሳምንታት በፊት ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ኬንያ፣ ሴኔጋልና ናይጄሪያ የነበሩ ሲሆን ከትናንት በስቲያም ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በድጋሚ መወያየታቸው ይታወቃል።

























