ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግሥት ወደ ትግራይ አልገባም ብሎ ያሳለፈው ውሳኔ ችግሩን ከጦርነት ውጭ ለመፍታት ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የሚፈፀመውን ወታደራዊ ዕርምጃ ላለመቀጠል መወሰኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ውሳኔው ከጦርነት ውጪ ያሉ ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን ለማጤን ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ብዙዎች በደስታ ተቀብለውታል የሉ ሲሆን አሁን ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት አደባባይ ነው ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።
አሜሪካ ግን ከዚህ የኢትዮጵያ አካሄድ በተቃራኒው መቆሟን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለሚደርስባት ግፊት አልንበረከክም በማለቷ የአሜሪካን አስተዳደር የሚያደርስባት ጫና መበርታቱንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የአሜሪካ መንግሥት አንዳንድ የችኮላ ውሳኔዎችን ወስኗል፤ በዚህም እናዝናለን ብለዋል።
የአሜሪካ አስተዳደርና የህግ አውጭ አካላት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ላይ በሚጥሏቸው ማዕቀቦችንና ዕርምጃዎች ከፍተኛ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

























