ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌደራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት አጠናቀቁ።
በዘመቻ ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት በተገኙ ድሎች፣ በታዩ ውስንነቶችና በቀጣይ ስለሚኖረው አቅጣጫ ለሦስት ቀናት ውይይት ሲካሄድበት የቆየው የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ግምገማዊ ሥልጠና በዛሬው እለት ተጠናቋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው በጦርነት የሚገኝ ድልን በአግባቡ መምራት ከጦርነቱ በኋላ ለሚመጣ መረጋጋትና ሰላም እንዲሁም ለዘላቂ የሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስምረውበታል፡፡
በዘመቻውም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ድል ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የህልውና ዘመቻው ያስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እጅግ አሳዛኝና የሀገር እዳ ቢሆንም ሂደቱ ግን በርካታ ትሩፋቶችን እንዳስገኘ አመራሩ መገምገሙ ተመልክቷል፡፡
አመራሮቹ ከድሎቹ ጋር የታዩና በቀጣይም ሊኖሩ ስለሚችሉ መልካም እድሎችና ዝንፈቶች በትኩረት መገምገማቸው የገለፁ ሲሆን ተናብቦና ተቀናጅቶ በአንድ አመራር ለአንድ ዓለማ የመስራት አቅም፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ሁለንተናዊ ህዝባዊ ተሳትፎና ተደጋግፎ ችግሮችን በጋራ መሻገርን እንዳስገኘ አመራሮቹ በግምገማ አዘል ስልጠናቸው ማረጋገጣቸው ተመልክቷል፡፡

























