ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በምሥራቅ ወለጋ ዞን የአባ ገዳዎችን ጥሪ የተቀበሉ 312 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጅ መስጠታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
እጃቸውን የሰጡት የቡድኑ አባላት አሸባሪው ሸኔ በአፉ ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለሁ ቢልም እስካሁን በወሰደው እርምጃ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፣ አካል ሲያጎድል፣ የሕዝብ ሀብት ንብረት ሲዘርፍ እና ሲያወድም ብቻ ማየታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በመነሳትም የያዝነው መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት አባ ገዳዎች ያደረጉልንን ጥሪ ተቀብለን ለመንግሥት እጃችንን ሰጥተናል” ብለዋል በሳሲጋ እና ዲጋቲ ወረዳዎች እጃቸውን የሰጡ የቡድኑ አባላት።
ይህ የጥፋት ኃይል በአንድ በኩል ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት እታገላለሁ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ እታገልልኻለሁ የሚለውን የኦሮሞ ሕዝብ አስገድዶ ገንዘብ እንደሚቀበለው እና ገንዘብ ያልሰጠውን ደግሞ በአሰቃቂ መንገድ እየገደለ መሆኑንም ተናግረዋል።
የእነርሱ ዓላማ ሕዝቡን አደኽይተው ለራሳቸው በአቋራጭ ለመክበር መሆኑን ተረድተናል፤ ሌሎች ወጣቶችም ይህንኑ ዓላማቸውን ተረድተው ራሳቸውን ከስህተት እንዲጠብቁ እንመክራለን” ብለዋል እጃቸውን የሰጡት ወጣቶች።
በዞኑ እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን 312 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጃቸውን መስጠታቸውን እንዲሁም 112 የተለያዩ መሣሪያዎች፣ ከ2 ሺህ 100 በላይ የተለያዩ ጥይቶች፣ ከአርሶ አደሩ የተዘረፈ 949 ኩንታል እህል፡ ከ600 በላይ ከብቶች እና ከ6 ሺህ በላይ ፍራሾች መያዛቸውን ኦቢኤን ዘግቧል።