ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከእስር ስለተፈቱ ግለሰቦች መግለጫ ሰጡ

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከእስር ስለተፈቱ ግለሰቦች መግለጫ ሰጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው ላሸነፈ ሽልማት፤ ለተሸነፈ ደግሞ በይቅር ለእኔ መንፈስ ምህረት መስጠት የታሪካችን ክፋይ ነው ሲሉ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ከቀደምት አባቶቻችን የምንማረው በጀግንነት ተዋግቶ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በይቅር ለእኔ መንፈስ ለተሸነፈ ምህረት ማድረግን ነው ብለዋል፡፡

አባቶቻችን ኢትዮጵያን በነጻነት ያቆዩት በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሰላምም በማሸነፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታና ምህረትን መስጠት የሚችለው ሁሌም አሸናፊ ወገን ነው ብለዋል፡፡

ከሰሞኑን ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦችን በሚመለከትም ውሳኔው ኢትዮጵያን በጽኑ አለት ላይ የሚያቆምና ዘላቂ ጥቅምና ሰላምን የሚያመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ውሳኔውን በሚመለከትም አንዳንዶቹ በቅንነት ሌሎቹ ደግሞ ሆነ ብለው ኢትዮጵያዊያንን ለማወክ ከፍተኛ ቁጣ ሲቀሰቅሱ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

በቅንነት “ለምን” ሲሉ የሚጠይቁ አካላት ኢትዮጵያን ከመውደድ መሆኑን እንደሚገነዘቡ ገልጸው እነዚህ አካላት ውሳኔው ኢትዮጵያን ይበልጥ አሸናፊ እንደሚያደርጋት ሊገነዘቡ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡

ውሳኔውም ክስ ማቋረጥ እንጂ ምህረት አለመሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች መንግስት የሰጣቸውን እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

LEAVE A REPLY