ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት በአማራ ክልል የሚተገበር የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ድርጅቱ ከለጋሽ አካላት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ትኩረቱንም የመተዳደሪያ አቅምን በማሳደግ፣ የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል እና የተቋማትን አቅም በማጎልበት ላይ አድርጎ ይሠራል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በሰሜን ወሎ ዞን እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን÷ በ207 ቀበሌዎች 217 ሺህ 879 ሰዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አለማየሁ ዋሴ÷ ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በየአካባቢው ካሉ የመንግሥት አካላት ጋር በመደጋገፍ ውጤታማ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸው÷ ሌሎች አካባቢዎችንም ለማልማት እየተሠራ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በግብርና ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ የገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊዋ መሠረት አዱኛ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለመንግሥት ተቋማት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ የመፈጸም አቅማቸውን እንደሚያሳደግና ቢሮውም ውጤታማነቱን በትኩረት እንደሚከታተል መግለፃቸው አሚኮ ዘግቧል፡፡