ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን የሚፈታ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን ለመፍታት መዘጋጀት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሁሉም ኃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ በብሔራዊ መግባባት ውይይቱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት መዘጋጀት ይገባቸዋል፡፡
ውይይት እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ መደረሱ በጣም ትልቅ እርምጃ ነው። ብሔራዊ ውይይቱ በአገራችን ኢትዮጵያ ከተከናወኑ ወሳኝ ነገሮች ከምርጫው፣ ከግድቡ መሞላት እና ከመንግሥት ምስረታው ባልተናነሰ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ብቻ ሳይሆን ሰላሳና አርባ አመታት ሲንከባለሉ የመጡ ምርጫ የማይፈታቸው ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ጉዳዮች በህገ መንግሥት፣ በፌዴራል አወቃቀር፣ በሰንደቅ አላማና በመሳሰሉት የሚገለጹና ፖለቲካው ሲስተካከል አብረው ይስተካከላሉ ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ተናግረዋል።