ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከውጪ የምናስገባቸውን የማዕድን ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራን ያለነው ስራ በፍጥነት በተግባር እየተገለፀ ይገኛል ሲሉ የማዕድን ሚኒስትር ኢ/ር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ከብረት አምራቾች ሙያተኞች ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ተውጣጥቶ ከተቋቋመ ሀገራዊ የብረት ምርት ስትሪግ ኮሚቴ ጋር ሥራው የደረሰበትን ሂደት መገምገማቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ የመጀመሪያ የቅድመ አዋጪነት ጥናት እና የፋብሪካ ግንባታ ቦታ መረጣ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ነው የገለጹት።
የብረት ምርትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካትም የሶስት ዓመት የፕሮጀክት ጊዜ መቀመጡ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱን የሚያስተባበር “ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት” በማዕድን ሚኒስቴር አስተባባሪነት መዋቀሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ስራውም በመንግስት ፣የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና በውጪ ባለሀብቶች በጋራ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።