ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ላይ በደረሰው የዝናብ መጨናገፍ የተነሣ፤ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች (ደ/ብ/ብ/ሕ)፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች ውስጥ ባሉ በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የከፋ ድርቅ የተከሠተ ሲሆን፤ ይህም የቤት እንስሳትን እና ሰብሎችን በማጥፋት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናትን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ችግር ቋፍ ገፍቷቸዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገለጸ።
የድርቁ ተጽእኖ እጅግ የከፋ ነው ያለዉ ድርጀቱ መተዳደሪያቸው እና እንስሳቶቻቸው ከጥቅም ውጪ ስለሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ለመትረፍ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ ብሏል።
እስከ መጋቢት 2014 ዓ. ም. መጀመሪያ ድረስ 6.8 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታን እንደሚፈልጉ የመረጃ ትንበያዎች እንደሚጠቁሙ ተገልጿል።
ደቡባዊ እና ምሥራቃዊ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ውስጥ ያሉት አካባቢዎች እጅግ የከፋ ተጽእኖ የደረሰባቸው አእንደሆኑ የገለጸዉ ዩኒሴፍ ጉልህ የሆነ የንጹህ ውሀ እጦት ከመኖሩም በላይ፤ የምግብ ዋስትና ደረጃው በፍጥነት እየተሟጠጠ በመሆኑ የምግብ እጥረት ክሥተቶች እየጨምሩ ይገኛል ብሏል በመግለጫዉ።
በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ውስጥ፤ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ 225 ሺህ ገደማ ሕፃናት እና ከ100 ሺህ የሚልቁ ነፍሰ-ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች አስቸኳይ የተመጣጠነ ምግብ ዕርዳታን ይሻሉ ተብሏል።
እስካሁን ድረስ በድርቅ በተጠቁት የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ውስጥ ባሉት አካባቢዎች ላይ በአሁኑ ወቅት በጽኑ የውሃ እጥረት የሚሰቃዩ 4.4 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዳሉም ተገለጿል።
በተጨማሪም በግጭት፣ በድርቅ፣ እና በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በመሳሰሉ በርካታ ምክንያቶች የተነሣ እ.ኤ.አ. በ2022 ላይ በአራቱ ክልሎች ያሉ 850 ሺህ ያህል የሚገመቱ ሕፃናት የከፋ የምግብ እጥረት እንደሚደርስባቸው የዩኒሴፍ የመረጃ ትንበያዎች ያመለክታሉ።
በድርቁ የተነሣ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ጭምርም እየተነጠሉ ነው። በቆላማው የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ውስጥ ያሉ ከ155 ሺህ የሚልቁ ሕፃናት ከትምህርት ቤት ቀርተዋል።
ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት፤ ዩኒሴፍ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በቅርብ በመቀናጀት፤ ነፍስ-አድን ዕርዳታዎችን በጽኑ ለሚሹት ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል።

























