ኢትዮጵያ በአረብ ሊግ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ ከሞሮኮ፣ ቱኒዝያና ኮሞሮስ ጋር ውይይት...

ኢትዮጵያ በአረብ ሊግ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ ከሞሮኮ፣ ቱኒዝያና ኮሞሮስ ጋር ውይይት ማድረጓ ተገለፀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሶስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት አቶ ደመቀ ከሶስቱ ሃገራት ጋር ባደረጓቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች፤ በአረብ ሊግ ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የአረብ ሊግ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚወስናቸው ለታችኞቹ የተፋሰስ አገራት የወገነ ውሳኔን በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና የአረብ ሊግ በቀጣይ የሚያወጣቸው መግለጫዎች የኢትዮጵያን፣ የሱዳንን እና የግብጽን የሶስትዮሽ ውይይቶች በሚያጎለብት መንገድ ሊቃኝ እንደሚገባው ኢትዮጵያ ማሳሰቧን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል። አምባሳደር ዲና በተለይም ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተደረገው ውይይት በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሃገራቱ በትብብር መንፈስ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳዩበት ነው ብለዋል።

በተለይ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሁለቱ ሀገራት በትብብር ለመስራት ከስምምት መደረሱንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከቱኒዚያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተደረገው ውይይትም በሁለቱ ሃገራት መካከል በግብርና፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና ቱኒዚያም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች ብለዋል፡፡

እንደአምባሳር ዲና ገለፃ፤ ቱኒዚያ ከዚህ ቀደም በአረብ ሊግ ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ አቋም መያዟን በተመለከተ በውይይቱ መነሳቱን ገልፀው ይህ ትክክል አለመሆኑንና በቀጣይ እንዲህ አይነት ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ቱኒዚያ መያዝ እንደማይገባት በውይይቱ መነሳቱን አብራርተዋል።

ሁለቱ ሃገራት በቀጣይ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራውንም አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል፡፡

LEAVE A REPLY