ዶ/ር ጢሞትዮስ እነ ስብኀት ነጋ የተፈቱት ሀገራዊ ጥቅምን ለማሰጠበቅ ነው አሉ

ዶ/ር ጢሞትዮስ እነ ስብኀት ነጋ የተፈቱት ሀገራዊ ጥቅምን ለማሰጠበቅ ነው አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተለያዩ መዝገቦች ጉዳያቸው በሕግ ሲታይ የነበሩ ግለሰቦች ክስ የተቋረጠው ስር እየሰደደ የመጣው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ እልባት እንዲያገኝና ሀገራዊ ጥቅምን ታሳቢ በማድረግ ነው ተባለ፡፡

በተለይ የሕወሃት ተባባሪ የነበሩትን ጨምሮ 6 ግለሰቦች ክስ መቋረጡ፣ ቡድኑ የሚነዛቸውን የሐሰትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በርኅራኄ ለማርከስ ታስቦ መኾኑን የፍትኅ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናግረዋል፡፡

የፍትኅ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የመሥሪያ ቤታቸውን የስድስት ወር የሥራ ክንውን ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አቅርበው ከአባላት ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ በሦስት መዝገቦች ጉዳያቸው በሕግ ሲታይ የነበሩ ግለሰቦች ክስ መቋረጡን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም ከነጀዋር መሐመድ ጋር በተያያዘ በሁለት መዝገቦች የተከሰሱት ሰዎች ክሳቸው የተቋረጠው በኢትዮጵያ ስር እየሰደደ የመጣውን ቅራኔና አለመግባባት ለመፍታት የታሰበው ሀገራዊ ምክክር አካታች ሆኖ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጥቅም እንዲያመጣ ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከ10000 የሚልቁ ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች መታሰራቸውን ጠቅሰው ፍትህ ለማምጣት ማሰርና መቅጣት ብቻውን በቂ ነው ብለን አናምንም ብለዋል፡፡

የሽግግር ፍትኅን ተግባራዊ ማድረግ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ጋር በተያያዘ ክሳቸው የተቋረጡ ስድስት ግለሰቦች ከእስር የተለቀቁት ደግሞ ሕወሓት በሀገርና በመንግሥት ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ለማቃለል ነው፡፡ በዚህም በሂደት ውጤቱ እየጠራ ይመጣል፤ አሁንም በጥቂቱ እየታየ ነው ብለዋል።

LEAVE A REPLY