ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ባወጣው የአቋም መግለጫ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ለተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ የመንግስት አመራር በከፊል ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆኑን ገለፀ።
አብን በመግለጫው በከፊሉ የመንግስት አመራር ደንታ ቢስነት እና በከፊሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ የመሆኑ ጉዳይ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል ብሏል።
አብን አሸባሪ ያለው የሸኔ ቡድን በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ከሰሞኑ በፈፀማቸው ጭፍጨፋዎች በወረዳው በተለያዩ አካባቢዎች 81 ወገኖቻችን ተግድለዋል፣ እንዲሁም በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ 87 ሰዎች በድምሩ 168 ወገኖች መገደላቸው ተረጋግጣል ብሏል። ግድያውንም የዘር ተኮር ጥቃት ብሎታል።
የአማራ ሕዝብ ፍላጎት በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በሰላምና በእኩልነት መኖር ብቻ ነው» ያለው አብን ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ፈጣንና አስተማማኝ ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አሳስቧል።
አብን በመግለጫው መላው ሕዝብ «በአፋር በኩል ላለው ግጭት ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ከአፋር ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ»ም ጥሪ አስተላልፏል። የፌድራሉ መንግስት ለአፋር ሕዝብ አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጥና እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በራያና ጠለምት ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ነው ያለው ድርብርብ ቀውስ አፋጣኝ መንግስታዊ ትኩረት እንደሚሻም አጥብቆ ጠይቋል።
የአብን መግለጫ በሕዝባችን ላይ ጥቃቱን የፈፀሙ አካላት በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡ እና ለተበዳዮች ካሳ እንዲከፈል ስንል እንጠይቃለን ሲል ገልጻል።