ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ድርጅቱ በሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለመጀመር ትናንት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል።
እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምረው የሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ህይወት ሽመልስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ትምህርት ቤቱ በአንድ ክፍል እስከ 120 ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ የመማሪያና አስተዳደር ክፍሎች ጥበት በተጨማሪ የውሃና የመጸዳጃ ቤት ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ችግር ተማሪ የመቀበል አቅሙን እንደገደበበትም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ያለው የግሎባል አሊያንስ ቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ፤ የትምህርት ቤቱን ችግሮች ለመፍታት የድርጅቱን አባላት በማስተባበር በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግሯል።
ግንባታው እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚፈጅና ሥራው በአፋር ልማት ማህበር በኩል የሚከናወን መሆኑን ጠቅሷል።
የአፋር ክልል ህዝብ ለሀገሩ ያለውን ዘመን የማይሽረው ታማኝነት በተግባር አስተምሮናል ያለው አርቲስት ታማኝ በየነ”በውጭ የምትኖሩ ወንድሞቼና እህቶቼ ወገናችሁ ለአገሩ እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በመረዳት በምንችለው ሁሉ ከአፋር ህዝብ ጎን ልንቆም ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
የአፋር ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኑረዲን ሰዲቅ በኩላቸው “ግሎባል አሊያንስና አርቲስት ታማኝ በየነ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ ብሏል።
ግብረሰናይ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የትምህርት ቤት የማስፋፊያ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለሁለት ብሎክና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንባታው በ8 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።