ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር የአፋር ክልል ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት አልተሰጠውም ሲል ወቅሷል። ተፈናቃዮቹ ባሉበት አስከፊ ሁኔታ የሞት አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጿል።
የማህበሩ አስተባባሪ የሆኑት ቫለሪን ብራውኒንግ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ” የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፍ ያንን ያህል አይደለም በዚያ ላይ በተበታተነ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት ይህም ሌላ ፈተና ነው ብለዋል ምግብ የለም ፣ ውሀ የለም ፣ አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ የሉም ያሉት አስተባባሪው። የተፈናቀሉት ሰዎች በረሃብ በጥማት እና በበሽታ ምክንያት የሞት ስጋት አንዣቦባቸዋልም። ” ብለዋል።
ማህበሩ በግመል እና በሌላም አማራጭ ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሞያዎች ቡድን አሰማርቶ ተፈናቃዮችን ለመድረስ ጥረት አድርጎ የነበር ሲሆን መድረስ የቻለው ግን ጥቂቶችን ብቻ ነው ብለዋል። በርካቶች ወደ መጠለያ ጣቢያ ለመምጣት ስጋት አለባቸው የሉት ብራውኒንግ ፥ ” ረጅም ርቀት የሚወነጨፉ ታንኮች እና ከባድ መሳሪያዎች ባስከተሉት ጉዳትና ይሄን ተከትሎ በፈጠረባቸው ጭንቀት ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ለመምጣት ይፈራሉ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በጦርነቱ አጥተዋል ብለዋል። በዚህም በጣም ጭንቀት ውስጥ በመሆናቸው ወደ አስፓልት መንገዶች አይወጡም፤ አንድ ላይ መሆን አይፈልጉም፤ በሚችሉት ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ለአደጋ ሳይጋለጡ የሚቆዩባቸውን ተግባር ነው የሚሰሩት ” ብለዋል።
የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ለሬድዮ ጣቢያው ገልጿል።